የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ተካሄዱ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ተካሄዱ
አዲስ አበባ ታህሳስ 132013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የሁለተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ተካሂደዋል።
የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ በ10 ክለቦች መካከል ከታህሳስ 10 ቀን 2013 ጀምሮ እየተካሄደ ነው።
የሊጉ ውድድሮች የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከልን መሰረት ባደረገ መልኩ ያለ ተመልካች እየተካሄዱ ነው።
ውድድሮቹ በባህርዳር፣ ሐዋሳና አዲስ አበባ ይካሄዳሉ።
የመጀመሪያዎቹ አራት ሳምንት ጨዋታዎች የሚካሄዱት ባህርዳር ላይ ነው።
በዚሁ መሰረት በሁለተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የእጅ ኳስ ሜዳ ተካሂደዋል።
ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማን 27 ለ 25 አሸንፏል።
በሌላ ጨዋታ የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታቸውን ያሸነፉት ፌዴራል ማረሚያ ቤቶችና ጎንደር ከተማ 25 አቻ በሆነ ውጤት ተለያይተዋል።
ውጤቱን ተከትሎም ፌዴራል ማረሚያ ቤቶችና ጎንደር ከተማ በተመሳሳይ ሶስት ነጥብ ይዘው በግብ ክፍያ ተበላልጠው አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ይዘዋል።
የሊጉ ሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገ በመቀጠል መከላከያ ከባህርዳር ከተማ እንዲሁም ከምባታ ዱራሜ ከፌዴራል ፖሊስ ይጫወታሉ።
በኢትዮጵያ የእጅ ኳስ ፌዴሬሽን የውድድር ደንብ መሰረት አንድ ጨዋታ የሚያሸንፍ ክለብ ሁለት ነጥብ የሚያገኝ ሲሆን፤ አቻ የወጣ ደግሞ አንድ ነጥብ ያገኛል።