ኢትዮጵያ ከተለያዩ አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት አጠናክራ ለመቀጠል ትሰራለች - ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከተለያዩ አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት አጠናክራ ለመቀጠል ትሰራለች - ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 13/2013 ( ኢዜአ) ኢትዮጵያ ከተለያዩ አገራት ጋር ያላትን ታሪካዊና ሁለንተናዊ ግንኙነት አጠናክራ ለመቀጠል እንደምትሰራ ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።
የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ የሰባት አገራት አምባሳደሮችን የሹመት ደብዳቤ ዛሬ ተቀብለዋል።
ፕሬዚዳንቷ የህንድ፣ የቻይና፣ የኮርያ፣ የጃፓን፣ የፓኪስታን፣ የቱኒዚያና የዙምባቤ አምባሳደሮችን ሹመት ነው የተቀበሉት።
በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ በተለይም በነበረው የሕግ ማስከበር ሂደት ዙሪያ ለአምባሳደሮቹ ገለጻ አድርገውላቸዋል።
ጎን ለጎንም ኢትዮጵያ ከአገራቱ ጋር ያላትን ለረጅም ጊዜ የቆየውን ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ የሁለትዮሽ ግንኙነቶች አብራርተውላቸዋል።
ይህም ግንኙነት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ፕሬዝዳንቷ ገልጸው በተለይም ከቻይና እና ከህንድ ጋር ያለው ኢኮኖሚያዊ አጋርነት መጠናከር እንዳበት ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ የጃፓንን የልማት መንገድ መከተል እንደምትፈልግና ከፓኪስታንም ጋር አጋርነቷን አሁን ካለበት ደረጃ ከፍ ለማድረግ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የአገራቱ አምባሳደሮችም ተመሳሳይ አቋም ማሳየታቸውን ውይይቱን የተከታተሉት የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገልጸዋል።
በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ከቱኒዚያና ዙምባብዌ ጋር ያላትን ግኝኙነት አጠናክራ መቀጠል እንደምትፈልግ ፕሬዝዳንቷ መናገራቸውን አምባሳደር ዲና ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት መሥራችና ለአህጉሪቱ ሕዝቦች ነጻነት የሰራች መሆኗን ጠቁመው በዚሁ መንፈስ አጋርነቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸዋል።
በደቡብ አፍሪካ አገራት ለነጻነት በሚደረገው ትግል ውስጥ የኢትዮጵያ ሚና ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠው መሆኑን ገልጸው፤ ከእነዚህም አገራት መካከል ዙምባብዌም ተጠቃሽ ነች ብለዋል።
የዙምብዌ የቅኝ አገዛዝ ሥርዓትን ለመገርሰስ ተሳታፊ የነበሩት የዙምባብዌ ዛኑና ዛፑ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ ሥልጠና መውሰዳቸውን በማስታወስ አስረድተዋል።
በተመሳሳይ ኢትዮጵያ የቱኒዚያም አጋር መሆኗን ገልጸው ፤ይህንን አጋርነቷን ለማስቀጠል በሁለቱም ወገን ቁርጠኝነት መኖሩን አምባሳደር ዲና ገልጸዋል።
አምባሳደሮቹ ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያከናወነችውን የሕግ ማስከበር ሥራ በተሳካ መልኩ ማጠናቀቋን አድንቀው በዚህ ጉዳይ አጋር ነን ብለዋል።
በመልሶ ማልማት ሥራ ላይም በተለይም የኮርያ መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ፍቃደኛ መሆኑን አምባሳደር ዲና አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሥራዋን በተሳካ መልኩ ለማስቀጠል ዝግጁ መሆኗንም አረጋግጠዋል።