የሃይማኖት አባቶች ሕሙማን የፀረ ኤች.አይ.ቪ ኤድስ መድሃኒት በአግባቡ እንዲወስዱ እንዲያስተምሩ ተጠየቁ - ኢዜአ አማርኛ
የሃይማኖት አባቶች ሕሙማን የፀረ ኤች.አይ.ቪ ኤድስ መድሃኒት በአግባቡ እንዲወስዱ እንዲያስተምሩ ተጠየቁ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 13/2013 ( ኢዜአ) የሃይማኖት አባቶች ሕሙማን የፀረ ኤች.አይ.ቪ ኤድስ መድሃኒት በአግባቡ እንዲወስዱ የማስተማር ሚናቸውን እንዲወጡ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ጠየቁ።
የሃይማኖት አባቶች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በመከላከል አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱም ተጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ሕሙማን የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መድሃኒት እንዲወስዱ የሚያስገነዝብበት የንቅናቄ መድረክ ዛሬ አካሂዷል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ የሃይማኖት ተቋማት ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን በመከላከልና በመቆጣጠር ያደረጉት አስተምህሮ ውጤታማ እንደነበር በመድረኩ አስታውሰዋል።
"በአሁኑ ወቅት ቫይረሱ የሌለ እስከሚመስል ድረስ በኀብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ መዘናጋት ይታያል" ያሉት ሚኒስትሯ የዕምነት ተቋማት ሚናቸውን እንዲጫወቱ ጠይቀዋል።
በተለይም ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ ዜጎች የጸረ ኤች.አይ.ቪ ኤድስ መድሃኒት ሳያቋርጡ እንዲወስዱ የአባቶች ሚና በመንፈሳዊ አገልግሎት እንዲጠናከር አሳስበዋል።
የሃይማኖት ተቋማት ከቫይረሱ ነጻ የሆነ ትውልድ መገንባት እንዲቻል ሃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
በተመሳሳይ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን መከላከል ላይ የሚታየው መዘናጋት ዋጋ እንዳያስከፍል የሃይማኖት አባቶች ማስተማር እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጠቅላይ ጸሃፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ በበኩላቸው ጉባዔው ሕሙማን የጸረ ኤች..አይ.ቪ ኤድስ መድሃኒት በመውሰድ የጤና ሁኔታቸውን ለማሻሻል እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል።
ከአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት ጋር በመተባበር ፕሮጀክት ቀርጾ ወደ ሥራ ለመግባት መዘጋጀቱንም ገልፀዋል።
ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ ሕሙማን ጥምረት ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር አቶ መኮንን ዓለሙ የጸረ ኤች.አይ. ቪ ኤድስ መድሃኒት የሚያቋርጡ ሕሙማን ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ገልፀዋል።
ይህም ሕሙማኑን ለከፍተኛ ጉዳት እየዳረገ ነው ብለዋል።
የጸረ ኤች.አይ.ቪ ኤድስ መድሃኒት መውሰድ ከሃይማኖት አስተምህሮ ጋር እንደማይጋጭ በማስተማር ግንዛቤ መፍጠር ይገባል ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከ667 ሺህ በላይ ዜጎች የኤች.አይ.ቪ ቫይረስ በደማቸው እንደሚገኝ መረጃዎች ያሳያሉ።