ቀጥታ፡

ሃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን ከሁለት ተቋማት ጋር ለመስራት ስምምነት ተፈራረመ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 13/2013 ( ኢዜአ) ሃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን ከኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣንና ከቱሪዝም ኢትዮጵያ ጋር መስራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ።

ፋውንዴሽኑ ከሁለቱ ተቋማት ጋር የተፈራረመው የመጀመሪያ ስምምነቱ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ላይ በጋራ መስራትን ዓላማ ያደረገ ነው።

ስምምነቱን የፋውንዴሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬና የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ ተፈራርመዋል።

ይህ ስምምነት የሚያተኩረው በአገሪቷ በሚገኙ በተመረጡ ስድስት ፓርኮች የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን በጋራ ማከናወን ላይ ነው።

በዋናነትም በፓርኮቹ ውስጥ የሚገኝ ስነ-ምህዳርና ብዝሀ-ሕይወት እንዲጠበቅ በማድረግ ዜጎች ከቱሪዝም ዘርፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መስራት የሚያስችልም ነው።

የፋውንዴሽኑ የቦርድ ሰብሳቢ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ የመንግስት ስራቸውን ሲለቁ ኅብረተሰቡን መጥቀም በሚችሉበት ዘርፍ ለመስራት ውጥን እንደነበራቸው ገልፀዋል።

ከባለቤታቸው ጋር ፋውንዴሽን በማቋቋም በእናቶችና ህጻናት ጤና፣ በስርዓተ ምግብ፣ በሴቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና በወጣቶች ስራ ፈጠራ እንዲሁም ዘላቂነት ያለው የአካባቢ ጥበቃና ቱሪዝም ልማት እየሰሩ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

አቶ ሃይለማርያም ፓርኮች እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ የሚገኙ በመሆኑ በውስጣቸው የሚገኝ ብዝሀ ህይወትን ለመታደግና ኅብረተሰቡም ከዚህ ተጠቃሚ እንዲሆን የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ስራ መከወን እንደሚገባ አንስተዋል።

ፋውንዴሽኑ ይህን የተፈጥሮ ሀብት ለመንከባከብ እንዲቻል ከባለስልጣኑ ጋር በጋራ ለመስራት ስምምነት ማድረጉን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ የሰው ልጅ ሕልውና መቀጠል የሚችለው የተፈጥሮ ሀብትን መጠበቅ ሲቻል መሆኑን ተናግረዋል።

ይህን እውን ለማድረግም የፓርኮች ሚና ከፍተኛ በመሆኑ የስምምነቱ አስተዋፅኦ ጉልህ መሆኑን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ ዜና የሃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን ከቱሪዝም ኢትዮጵያ ጋር የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ በጋራ ለመስራት ስምምነት ተፈራርሟል።

የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ግርማ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ስምምነቱ በኢኮ ቱሪዝም ላይ በጋራ በመስራት ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ ያለመ ነው ብለዋል።

በዘርፉ የውጭ ባለሀብቶችና የፋይናንስ ተቋማት የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን እንዲያለሙ በመጋበዝ በርካታ የስራ ዕድል ፈጠራና ሌሎችም ስራዎች መስራት ይቻል ዘንድ ስምምነት መፈረሙን ጠቁመዋል።

ሃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን በቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝና ባለቤታቸው ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬ የተመሰረተ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም