ቀጥታ፡

በጸጥታ መዋቅሩ ዘርፍ የተደረገው ሪፎርም የሀገር ሉአላዊነትን የሚያስጠብቅ ነው- የቀድሞ የደህንነት ዘርፍ አማካሪ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ

ታህሳስ 13/ 2013 ( ኢዜአ) በጸጥታ መዋቅሩ ዘርፍ የተደረገው ሪፎርም ህገ መንግስቱን መሰረት ያደረገና የሀገር ሉአላዊነትን የሚያስጠብቅ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀድሞ የደህንነት ዘርፍ አማካሪ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ ገለጹ።

አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አማካኝነት በሚዘጋጀው 'ፖሊሲ ማተርስ' ዝግጅት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ከሪፎርሙ በፊት በመከላከያ፣ በፖሊስ እና በመረጃና ደህንነት መስሪያ ቤት ባልደረቦች የሰብአዊ መብት ሲጣስ እንደነበር አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ህዳር 21/2013ዓ.ም ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ያቀረቡትን ማብራሪያ መሰረት አድርገው እንደገለጹት ህገመንግስቱ ከምንም በላይ ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው ሰብአዊ መብቶች ላይ ሆኖ እያለ በመከላከያ በፖሊስ እና በመረጃና ደህንነት መስሪያቤት ባልደረቦች አልተከበረም ።

አቶ ተስፋሁን ላለፉት በርካታ አመታት ለቁጥር የበዙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችና ግድያዎች ተፈጽመዋል ነው ያሉት።

የብሄራዊ መረጃና ደህንነት እና የመከላከያ ከፍተኛ ሃላፊዎች በህግ ከተሰጣቸው ስልጣን እና ሃላፊነት ውጪ በክልሎች አስተዳደር ላይ ጣልቃ ሲገቡና ያሻቸውን ሲፈጽሙ ነበር ብለዋል።

በመሆኑም የጸጥታና ደህንነት ድርጅቶች ጥፋቶችና የመብት ጥሰቶች የሚከላከሉባቸውና ስህተቶች የሚታረሙበት ጠንካራ ህግና ስርአት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

አቶ ተስፋሁን ለውጡን ተከትሎ ከፍተኛ ሪፎርም ያስፈልጋቸዋል ከተባሉ ዘርፎች መካከል የብሄራዊ ደህንነት አንዱና ዋነኛው በመሆኑ “ፀጥታና ደህንነት” የሚለውን አስተሳሰብ ድጋሚ መበየን አስፈላጊ ነበር ብለዋል።

የደህንነት ስራ በዜጎች ሁለንተናዊ ጥቅም የሚሰራ እንደሆነ ዜጎች እንዲገነዘቡት የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት ስለመከናወናቸው ያብራሩት አቶ ተስፋሁን፤ የደህንነት ባለሙያዎችን አቅም ለመገንባት የእይታ አድማሳቸውን የሚያሰፉባቸውን ስልጠናዎች ማቅረብና ከሰብአዊ መብቶች ጥበቃና ተያያዥ ጉዳዮች አኳያ ተጠያቂነትን ማስፈን የሚያስችሉ የአሰራር ስርአቶች መዘርጋታቸውን ገልጸዋል።

ከሪፎርሙ በፊት በመከላከያ ሰራዊቱ አደረጃጀትና የሰራዊቱ የስልጠና ሰነዶች ህገመንግስታዊ ካለመሆናቸውም በላይ የሰራዊቱን ስም የሚያጠለሽ ብሎም ከብክነት ከሙስናና ሌሎች ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች የሚነሱበት እንደነበር አስታውሰዋል።

በዚህም ከሪፎርም በፊት በነበሩ አመታት በርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችና ግድያዎች በዜጎች ላይ የተፈጸሙ ሲሆን በምልመላ በስንብት እንዲሁም በጡረታ ስር የሰደዱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ነበሩ ነው ያሉት።

ለውጡን ተከትሎ የተዘጋጀው የሰራዊቱ ሰነድ ማንም ዜጋ ሰራዊቱን መቀላቀል ቢፈልግ ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ነጻ ሆኖ መገኘት እንዳለበት ሃገሪቱ ስለሚኖራት የሰው ሃይል፤ የመሳሪያ፤ የቴክኖሎጂ እና የገንዘብ አመዳደብ ያሉ ግልጽ መመሪያዎችን ስለማካተቱ አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም