ቀጥታ፡

በሰኔ 16ቱ የድጋፍ ሰልፍ ፍንዳታ ተጠርጣሪዎች ላይ ተጨማሪ የሰባት ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ተፈቀደ

አዲስ አበባ ሐምሌ 13/2010 ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም በነበረው የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የድጋፍ ሰልፍ ላይ በደረሰ ፍንዳታ በቁጥጥር ስር በዋሉ ተጠርጣሪዎች ላይ ተጨማሪ የሰባት ቀናት ጊዜ ቀጠሮ ተፈቀደ። ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ድጋፍ ለመስጠት ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ በወጣው ሕዝብ ላይ በደረሰው የቦምብ ፍንዳታ የተጠረጠሩ የጸጥታ አካላትና ሲቪል ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየታዬ መሆኑ ይታወሳል። በዚህም 'ኃላፊነታቸውን አልተወጡም' በሚል የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሸነር የነበሩት ግርማ ካሳን ጨምሮ ዘጠኝ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አባላትና በጥቃት አድራሽነት የተጠረጠሩ ግለሰቦች ልደታ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት 10ኛ ወንጀል ችሎት ለሶስተኛ ጊዜ ዛሬ ቀርበዋል። የወንጀል ምርመራ ቡድኑ ከዚህ በፊት የቀሪ ምስክሮችና ተከሳሽነት ቃል መቀበል፣ ከክልሎች ምስክሮችን ማምጣት፣ ያልተያዙ ተጠርጣሪዎችን መያዝ፣ ለምርመራ የተሰጡ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን ውጤት መቀበልና አሻራ መቀበል በሚል በጠየቀው የተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ መሰረት ችሎቱ የምርመራ ውጤቱን ይዞ እንዲቀርብ ለዛሬ ሐምሌ 13 ቀን 2010 ዓ.ም ቀጠሮ ይዞ ነበር። የምርመራ ቡድኑ በተሰጡት የምርመራ ቀናት ውስጥ በርካታ የምርመራ ስራዎችን ማከናወኑን ገልጾ፤ አሁንም ለተጨማሪ የሰነድ ማስረጃ፣ የአሻራ ምርመራና የምስክርነት ቃል ለመቀበል የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጠይቋል። ተጠርጣሪዎች በበኩላቸው መርማሪ ቡድኑ ያቀረበው ተጨማሪ ጊዜ መፈቀድ እንደሌለበትና ተጠርጣሪዎቹ በውጭ ሆነው ጉዳያቸውን ቢከታተሉ በምርመራ ሂደቱ ላይ የሚያደርሱት ተዕፅኖ እንደሌለ በመገለጽ፤ የዋስትና ሕገ መንግስታዊ መብታቸው ተጠብቆ እንዲለቀቁ ጠይቀዋል። ግራ ቀኙን ያደመጠው ችሎቱም ተጠርጣሪዎቹና ጠበቆቻቸው ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ መርማሪ ቡድኑ በአንድ ሳምንት ውስጥ ቀሪ ስራዎችን አጠናቆ እንዲቀርብ የሰባት ቀናት የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል። በዚህም ችሎቱ በሁለት መዝገብ ጉዳያቸው እየታየ ያሉ ተጠርጣሪዎችን ጉዳይ ለመስማት ለሐምሌ 20 ቀን 2010 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም