ቀጥታ፡

በአብሮነትና ወንድማማችነት መርህ የተመሰረተውን የኢትዮጵያ እና የሱዳን ህዝቦች ግንኙነት በኢኮኖሚያዊ ትስስር ማጠናከር ይገባል...አቶ ደመቀ መኮንን

ታህሳስ 13/2013 ( ኢዜአ) በአብሮነትና ወንድማማችነት መርህ የተመሰረተውን የኢትዮጵያ እና የሱዳን ህዝቦች ታሪካዊ ግንኙነት በሁለትዮሽ ኢኮኖሚያዊ ትስስር ማጠናከር እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አስታወቁ።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የተመራ ልዑክ በኢትዮጵያ እና ሱዳን የጋራ የድንበር ኮሚቴ ውይይት ላይ ለመታደም ዛሬ ሱዳን ካርቱም ገብቷል፡፡

በልዑኩ የመከላከያ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ቀንዓ ያደታ እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነት አማካሪ ገዱ አንዳርጋቸው ተካተዋል።

በዚህ ወቅት አቶ ደመቀ ሱዳን ሽብርን ከሚደግፉ አገራት ዝርዝር በመሰረዟ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው ፤ሱዳን ከእንደዚህ አይነቱ ዝርዝር መሰረዟ ለአገሪቱም ሆነ ለቀጠናው ልማታዊ ስኬት ከፍተኛ አስተዋትኦ ያበረክታል ብለዋል።

በድንበር አካባቢ የሚካሄድ የንግድ ግንኙነት በአካባቢው ላይ የሚኖሩ ዜጎችን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ በድንበር አካባቢ ላለው ደህንነትና ሰላም መጠበቅ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለውም ጠቁመዋል።

በሁለቱ ሀገራት የጋራ ግንባር ከጥቅምት 30 ጀምሮ የሱዳን ወታደሮች በተጠናከረ ሁኔታ በከፍተኛ መሳሪያ ጥቃት መፈጻማቸውን፣ በርካታ ንጹሃን መሞታቸውንና መቁሰላቸውንም አስታውቀዋል።

በዚህም የኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮች ግብርና ምርቶች መዘረፋቸውን ፣ ጎተራዎቻቸው መውደሙን አስታውሰዋል።

አብሮነትና ወንድማማችነት የሱዳንና ኢትዮጵያ የሁለትዮሽ ግንኙነታችን መርህ ከሚገለጹበት መንገድ አንዱ መሆኑን በመገንዘብ የኢትዮጵያ ብልጽግና ለሱዳን የሱዳን ብልጽግና ለኢትዮጵያ ወሳኝ መሆኑን ማወቅ ይገባል ብለዋል።

የአንዱ ወገን መሻሻል ለሌላው መሻሻል መነሻ እንደመሆኑ በተቃራኒው የአንድ ወገን መጎዳትም ለሌላው ጉዳት መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

“በቅርቡ በጋራ ድንበራችን ላይ የተከሰተው ሁኔታ በአብሮነትና በወንድማማችነት መርህ የተመሰረተውን የሁለትዮሽ ግንኙነታችን የሚያሻክር አይደለም” ብለዋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ።

ባለፈው ሰኔ ወር ላይ ሁለቱ አገራት ካደረጉት የጋራ የሰላም ስምምነት ባፈነገጠ መልኩ ይህ ጥቃት መፈጸሙን አመልክተው፤ የጋራ ችግሮችን በዘላቂ ሁኔታ ለመፍታት በድንበር ላይ ባሉ የሰፈራ ቦታዎችና፣ የእርሻ ስፍራዎች ላይ እርቀ-ሰላም ብቸኛው መፍትሄ ነው ብለዋል።

በድንበር አካባቢም አላስፈላጊ ጦር ማስፈር ሁኔታውን ከማባባስና ውጥረትን ከመፍጠር ባሻገር በድንበር አካባቢ የሚኖሩት ህዝቦች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ እንደሚያደናቅፍ ተናግረዋል።

ሁልጊዜም የኢትዮጵያ እና የሱዳን ግንኙነት ምልክት በሆነው ወንድማዊ ትብብር እና ቁርጠኝነት ችግሩ እንደሚፈታ እምነታቸው መሆኑን ነው የገለጹት።

በሁሉም የሁለትዮሽ ፣ አካባቢያዊ እና ሁለገብ የጋራ ጉዳዮች መንግሰት ከሱዳን ሪፐብሊክ መንግስት ጋር በቅርበት ለመስራት ጽኑ አቋም እንዳለው አረጋግጠዋል፡፡

የሁለቱን ወንድማማች ህዝቦች ተጠቃሚ የሚያደርግ ኢኮኖሚያዊ ትስስርና ሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ለዚህም በያዝነው ሳምንት የትራንስፖርት ሚኒስትሯ በሁለቱ አገራት መካከል የሚገነባውን የወደብ ማስፋፊያና የባቡር መስመር ግንባታ አስመልከቶ ከሱዳን መንግሰት ጋር እንደሚወያዩ ጠቁመዋል።

የአገራቱን የንግድና የኢንቨስትመንት ፍሰት በማሳለጥ ረገድ እሙን ነው ብለዋል።

ባሳለፍነው ጥቅምት ወርም የሱዳን የቢዝነስ ልዑክ በኢትዮጵያ በመገኘት ሁለቱን አገራት በዘርፉ ተጠቃሚ የሚያደርግ የጋራ ምክክር መደረጉን ጠቁመዋል።

ከሃያ አመታት በፊት የተፈረመው ፕሮቶኮል ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተገናዝቦ እንዲሻሻል ለውይይት መቅረቡ ሰፊ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።

በሌላ በኩል አቶ ደመቀ መኮንን እ.ኤ.አ ጥር 2021 ስራ የሚጀምረው የአፍሪካ ነጻ ቀጠናዊ ንግድ አፍሪካውያንን በሰፊው ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም