ለአምራች ኢንዱስትሪው 5 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር የሊዝ ፋይናንስ ብድር ተመቻቸ - ኢዜአ አማርኛ
ለአምራች ኢንዱስትሪው 5 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር የሊዝ ፋይናንስ ብድር ተመቻቸ
አዲስ አበባ ታህሳስ 13/2013 (ኢዜአ) ለአምራች ኢንዱስትሪው 5 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የሊዝ ፋይናንስ ብድር መመቻቸቱን የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለስልጣን አስታወቀ።
ብድሩ ከፊታችን ጥር ወር ጀምሮ በኢትዮጵያ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ለተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች እንደሚሰጥ ተገልጿል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አስፋው አበበ እንዳሉት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ያመቻቸው የሊዝ ፋይናንስ ብድር ለኢንተርፕራይዞቹ ይሰጣል።
በዚህም ለአምራች ኢንዱስትሪው 5 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የሊዝ ፋይናንስ ብድር ተመቻችቷል ብለዋል።
ብድሩ አምራች ኢንዱስትሪው ለሚያጋጥመው የፋይናንስ እጥረት እፎርታ የሚሰጥና ለማሽነሪ ግዥና ለስራ ማስኬጃ እንደሚውል መሆኑንም አመልክተዋል።
ወደ ስራ ለማስገባት የአሰራር መመሪያዎች መዘጋጀታቸውንና በተለይም የፋይናንስ እጥረት ያጋጠማቸው ኢንዱስትሪዎች ቅድሚያ ይሰጣቸዋል ተብሏል።
የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለስልጣን የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የፌዴራልና የአዲስ አበባ አስተዳደር የተለያዩ ተቋማት ሥራ ኃላፊዎች ታድመዋል።