የአማራ ክልል የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ጉባኤ ዛሬ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት ተጀመረ

ጎንደር ሀምሌ 13/2010 በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች በስርአተ ትምህርት ቀረጻ፣ በተማሪዎች ምዘናና በማጠናከሪያ ትምህርት አሰጣጥ ወጥ የሆነ የአፈጻጸም መመሪያ እንዲኖራቸው እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ፡፡ 17ኛው በአማራ ክልል የሚገኙ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም ጉባኤ ዛሬ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት ተጀምሯል፡፡ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዘዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን በጉባኤው እንደተናገሩት በአማራ ክልል 10 ነባርና አዲስ ዩኒቨርሲቲዎች የተማሪዎቻቸውን እውቀትና ክህሎት ለማጎልበት እየሰሩ ይገኛል፡፡ ፎረሙ ዩኒቨርሲቲዎቹ ከተናጥል ይልቅ በጋራ የሚሰሩበትን ሁኔታ በማመቻቸት በተለይ በስርአተ ትምህርት ቀረጻ የሚታዩ ጉድለቶችን በመፈተሽና ክፍተቶችንም በመለየት ወጥ አሰራር የሚከተሉበትን መመሪያ ማዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡ በቀደመው አሰራር ዩኒቨርሲቲዎቹ አዳዲስ የትምህርት ኘሮግራሞችን ሲከፍቱ ምን ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት እንዳለባቸው በግልጽ የተቀመጠ የአሰራር መመሪያ እንዳልነበረ ገልፀዋል፡፡ እንዲሁም በዩኒቨርሲቲዎቹ የተማሪዎች የምዘና ውጤት አሰጣጥ ወጥነት የጎደለው እንደነበር ያመለከቱት ምክትል ፕሬዘዳንቱ ለአብነተም 50፣ 60 እና 70 ከመቶ የምዘና ውጤት የሚሰጡ ዩኒቨርሲቲዎች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ ይህ ወጥነት የሌለው የተማሪዎች የምዘና ውጤት አሰጣጥ በተማሪዎች ዘንድ ቅሬታን ከመፍጠር ባለፈ የመልካም አስተዳደር ችግር እየሆነ በመምጣቱ ፎረሙ አንድ ወጥ መመሪያ አንዲዘጋጅ እያደረገ ነው፡፡ የማጠናከሪያ ትምህርት አሰጣጥም ቢሆን ትምህርት ሚኒስቴር ያዘጋጀው ሀገር አቀፍ መመሪያ ቢኖርም አተገባበሩ በዩኒቨርሲቲዎች ልዩነት መኖሩን አመልክተዋል፡፡ ፎረሙ በ2010 የትምህርት ዘመን በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በጋራ ሆነው የሚሰሩበትን ወጥ መመሪያ በማዘጋጀት ተግባራዊ የሚሆንበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ የደብረታቦር ዩንቨርሲቲ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዘዳንት ዶክተር መንበሩ ተሾመ በበኩላቸው በአማራ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ የሚታዩ ክፍተቶች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲዎቹ የማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮጀክቶች ሲቀረጹ በአገልግሎት ሰጪና ተቀባይ መካከል ወጥነት ያለው አሰራር አለመኖሩን ጠቁመዋል፡፡ በምርምሩ ዘርፍ በፈጠራ ስራ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ግለሰቦች ወጥ የሆነ የማበረታቻ ክፍያ ስርአት አለመኖሩን ገልፀው ፎረሙም ክፍተቶችን በመለየት አንድ ወጥ አሰራር የሚፈጠርበትን መመሪያ እንደሚያዘጋጅ እምነታቸውን ገልፀዋል፡፡ የጎንደር ዩንቨርሲቲ ፕሬዝዳንትና የፎረሙ ሰብሳቢ ዶክተር ደሳለኝ መንገሻ በፎረሙ መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት ''ፎረሙ የክልሉን ዩኒቨርሲቲዎች በጋራ በማስተባበር ተልዕኮአቸውን በብቃት የሚወጡበት ሁኔታ ማመቻቸት ነው'' ብለዋል፡፡ ለሁለት ቀናት በሚቆየው የፎረሙ ጉባኤ ላይ በክልሉ ከሚገኙ 10 ዩኒቨርሲቲዎች የተጋበዙ ፕሬዝዳንቶችና ምክትል ፕሬዝዳንቶች እንዲሁም የትምህርት ባለሙያዎችና የክልል አመራሮች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ ጉባኤው ፎረሙ ባዋቀራቸው ኮሚቴዎች ጥናት ተደርጎባቸውና የማሻሻያ ሃሳብ ታክሎባቸው በተዘጋጁ መመሪያዎች ላይ የጋራ ውይይትና ምክክር በማድረግ በቀጣዩ አመት ስራ ላይ የሚውሉበትን ሁኔታ ያመቻቻል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም