የቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ቅዳሜ ይካሄዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
የቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ቅዳሜ ይካሄዳሉ
አዲስ አበባ ግንቦት 1/2010 የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የ2010 ዓ.ም የሁለተኛ ዙር ሶስተኛ ጨዋታዎች ቅዳሜ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ይካሄዳሉ። በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከወልቂጤ ከተማ ከረፋዱ አራት ሰዓት ተኩል እንዲሁም ኢትዮጵያ ውሃ ስፖርት ከየካ ክፍለ ከተማ ከረፋዱ አምስት ሰዓት ተኩል ላይ ይጫወታሉ። በክልል ከተሞች ድሬዳዋ ላይ ድሬዳዋ ከተማ ከአዳማ ከተማና ጎንደር ከተማ ከሃዋሳ ከተማ በተመሳሳይ ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ላይ የሚጫወቱ ይሆናል። በ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ የሴቶች ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የሁለተኛ ዙር ሶስተኛ ጨዋታ ቅዳሜ በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከወልቂጤ ከተማ ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ላይ ይጫወታሉ። በዚህ ሳምንት በወጣው መርሃ-ግብር የፌዴራል መንግስት ቤቶች ኮርፖሬሽን ከአማራ መንገድና ህንጻ ዲዛይን ጨዋታቸውን ማድረግ የነበረባቸው ቢሆንም የፌዴራል መንግስት ቤቶች ኮርፖሬሽን ከውድድሩ ውጭ በመሆኑ ጨዋታው አይካሄድም። በኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ስምንት ቡድኖች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ። የፌዴራል መንግስት ቤቶች ኮርፖሬሽን ያለፉትን ሁለት የሊግ ጨዋታዎች ሳይጫወት በመቅረቱ ፎርፌ የተሰጠበት በመሆኑ በህጉ መሰረት በሁለት ተከታታይ ጨዋታ ፎርፌ የተሰጠበት ቡድን ከውድድሩ ውጭ ይሆናል ስለሚል ቤቶች ኮርፖሬሽን ከሊጉ ተሰናብቷል። በዚህም ምክንያት አምስት ቡድኖች ይሳተፉበት የነበረው የኢትዮጵያ የሴቶች ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ወደ አራት ዝቅ ያለ ሲሆን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ወልቂጤ ከተማ፣ አማራ መንገድና ህንጻ ዲዛይን እና ጎንደር ከተማ የሊጉ ተሳታፊ ክለቦች ናቸው