ቀጥታ፡

በሰንበቴ ከተማ ከ39 ሺህ ብር በላይ ሀሰተኛ የብር ኖቶች የተገኘባቸው ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

ደሴ ታህሳስ 13 /2013( ኢዜአ) በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ሰንበቴ ከተማ ከ39ሺህ ብር በላይ ባለ 200 ሀሰተኛ የብር ኖቶች የተገኘባቸው ሁለት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ፖሊስ አስታወቀ።

የወረዳው ፖሊስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር መሃመድ አሊ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ተጠርጣሪዎቹ ትናንት ቀን በከተማዋ ገበያ ቦታ ሁለት ሠንጋዎችን በ29 ሺህ 400 ብር በመግዛት ከፍለው ሊሄዱ ሲሉ ሻጮች ብሩን በመጠራጠራቸው ለፖሊስ ጥቆማ በመስጠታቸው ሊደረስባቸው ችሏል።

ፖሊስም ባደረገው የማጣራት ሥራ ብሩ ሃሰተኛ መሆኑን በማረጋገጡ ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ሥር በማዋል ባደረገው ፍተሻ ተጨማሪ 10ሺህ ሃሰተኛ የብር ኖት ማገኘቱን ተናግረዋል።በአሁኑ ወቅት ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ተይዘው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝ ዋና ኢንስፔክተሩ አስረድተዋል፡፡

ከአንድ ወር በፊትም 6 ሺህ ሐሰተኛ ባለ 200 የብር ኖቶች በመያዝ ህብረተሰቡን ለማጭበርበር የሞከረ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ማዋሉንም አስታውሰዋል።

ህብረተሰቡ በብርም ሆነ ሌሎች አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥመው በአካባቢው ለሚገኙ የጸጥታ አካላት እንዲጠቁምና ሀሰተኛ የብሩን ኖት ለመለየት ግብይት ከመፈጸሙ በፊት ለሚያውቅ ሰው በማሳየት ከመጭበርበር መዳን እንደሚችልም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም