ቀጥታ፡

ሀገራዊ ለውጡ የተሻገራቸው ፈተናዎች

ገዛኸኝ ደገፉ (ኢዜአ)

ባለፉት ሁለት አስር አመታት ሀገራችን በብዙ አዎንታዊና አሉታዊ ሁኔታዎች ውስጥ አልፋለች። የፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር፣ ቋንቋና ባህሎቻቸውን የማሳደግ፣ የመደራጀትና ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት፣ የመምረጥና የመመረጥ መብትና የመሳሰሉት በህገ መንግስቱ ዋስትና እንዲያገኙ ተደርጓል። በኢኮኖሚና ማህበራዊ መስኮችም ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎች ታይተዋል። ይሁን እንጂ በህገ መንግስቱ ላይ ዋስትና እንዲያገኙ የተደረጉ መሰረታዊ ጉዳዮች በተግባር ተቃርኖ ፈጥረው ቆይተዋል።

በኢፌዴሪ ህገ መንግስት መግቢያ ላይ የተደነገገው “አንድ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ግንባታ” ላይ ትልቅ ክፍተት እንደነበር ባለፉት ዓመታት የነበሩትን ሁኔታዎች ማስተዋል በቂ ነው። ከሀገራዊ ለውጡ በፊት በነበረው ብሔር ተኮር ፖለቲካዊ ሁኔታ ምክንያት ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች የጋራ በሚያደርጋቸው እሴቶች ዙሪያ ከማተኮር ይልቅ ልዩነታቸው ላይ ተጠምደው እንዲቆዩ ተገደዋል። ይህም አንደኛው ወገን በዳይ ሌላኛው ደግሞ ተበዳይ እንዲመስሉ አድርጓቸዋል። በሀይማኖቶች መካከልም እርስ በርስ እንዲሁም አንዱ ሌላውን የማይተማመኑበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር።

በተለይ ከምርጫ 1997 ወዲህ ያሉ ዓመታት በብዙ ኢትዮጵያውያን አእምሮ ውስጥ ጥቁር ነጥብን የጣሉ ነበሩ። በወቅቱ የተፈጠረው ክስተት ዳግም ምርጫ የሚባል ነገር ባልመጣ የሚያስብል ነበር። ምርጫ ቆጠራው እስከ ተደረገበት ሰዓት ድረስ ሰላማዊ የነበረ ቢሆንም ከቆጠራው በኋላ ከገዢው ፓርቲም ይሁን ከተፎካካሪ ፓርቲዎች የተሰጡት አስተያየቶች ዋጋ አስከፍሏል፡፡  በምርጫው ውጤት ሳቢያ በተቀሰቀሰ አመፅ በሰኔ ወር 1997 ዓ.ም እና በህዳር ወር 1998 ዓ.ም ውስጥ ብዙዎች ለህልፈት ተዳርገዋል፣ ብዙዎቹ አካል ጉዳተኛ ሆነዋል፣  ንብረት ወድሟል። የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን ጨምሮ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችም በተደረገ የቤት ለቤት አሰሳ ለእስር ተዳርገዋል፡፡

በዜጎች ላይ የደረሰውን የአደጋ መጠን ለማጣራት የተቋቋመው አጣሪ ኮሚሽን ባወጣው ሪፓርት መሰረት ወደ 200 የሚሆኑት ዜጎች ለሞት መዳረጋቸውን እና ከነዚህም ውስጥ 40 የሚያህሉት ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት እንደነበሩ ተገልጿል። ከዚህ በኋላ የወጡ ህጎች በተለይም የጸረ ሽብርተኝነት ህጉ ችግሩን ይበልጥ እንዲባባስ አድርጎታል።

የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የመልማት ፍላጎት፣ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት፣ የነፃነትና የእኩልነት ጥያቄዎች በየጊዜው እየተነሱ የነበረ ቢሆንም መሰረታዊ ምላሽ ሊያስገኙ አልቻሉም። ተቃውሞው እየሰፋና እየበረታ መጥቶ ከሁለት ዓመታት በፊት ሀገራዊ ለውጥ እንዲጀመር አስገድዷል።  ሀገራዊ ለውጡ እንደተጀመረ አዳዲስ የመፍትሔ እርምጃዎች በፍጥነት ተወስደዋል። የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን ጨምሮ በርካታ እስረኞች ከማረሚያ ቤት እንዲለቀቁ ተደርጓል። በሀይማኖቶች መካከል የነበረው እርስ በርስ መጠራጠርና አለመተማመን እልባት እንዲያገኝ ተደርጓል።  በውጭ ሀገር የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አክቲቪስቶች ወደ ሀገር ቤት እንዲገቡ ከመደረጉም ባሻገር ብዙዎቹ አፋኝ የነበሩ ህጎች ተሻሽለዋል። የፍትህ ተቋማት በነጻነት እና በገለልተኛነት እንዲያገለግሉ የሚያስችል ለውጥና ማሻሻያ ተደርጎባቸዋል። የምርጫ ህግም በአዲስ መልክ እንዲዘጋጅ ተደርጎ የተቋም ሪፎርም ተካሂዷል። ለውጡን ተከትሎ የተወሰዱ የመፍትሔ እርምጃዎች ለሀገሪቱ አዲስ ምእራፍ የከፈተ እንደሆነ በኢትዮጵያውያንና ለውጡን በተገነዘቡ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ይነገርለታል።

“ፍሪደም ሃውስ” የተባለው ተቋም ከሁለት አመታት በፊት ባስነበበው ሰፊ ሃተታ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የመገናኛ ብዙሃን የሚዲያ ነጻነትን ለማረጋገጥ፣ ነጻና ገለልተኛ ተቋማትን ለመመስረት እንዲሁም በአፋኝ ህጎችን ላይ ማሻሻያ በማድረግ የጀመሩት ሀገራዊ ሪፎርም ወደተሻለ ምእራፍ የሚያሸጋግር ስለመሆኑ አመልክቶ ነበር። በዲሞክራሲ ተቋማት ግንባታ ዙሪያ የተሰሩ የሪፎርም እርምጃዎች፣ የጸጥታ አካላት ገለልተኝነትና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎች ስኬታማ ስለመሆናቸውም አውስቷል።

ሀገራዊ ለውጡ አዲስ ተስፋን የፈነጠቀውን ያህል ያስገኛቸው ውጤቶችና ያለማቸው ራእዮች በተጀመረው ፍጥነት ወደ ተግባር እንዳይሸጋገሩ ያደረጉ ተግዳሮቶች ባለፉት ሁለት ዓመታት ተስተውለዋል። ከሀገራዊ ለውጡ ዋዜማ ጀምሮ ደስተኛ ያልነበረው ህወሃት ቡድን ተግዳሮቶቹን በማብዛት ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳል። የፌዴሬሽን ምክር ቤት “የህወሓት ኢ-ሕገመንግስታዊ እንቅስቃሴና ፌዴራላዊ ስርዓቱን ለማዳን የተደረጉ ጥረቶች” በሚል ርእስ ለውይይት ባዘጋጀው ሰነድ ላይ እንደተገለጸው የሕወሃት አመራር በለውጡ ዋዜማ በአንድ በኩል በሰላማዊ የሐሳብ ትግል ውስጥ እየተሳተፈ እንዳለ እያስመሰለ በሌላ በኩል ደግሞ የመንግሥትን የደኅንነትና የጸጥታ መዋቅር ተጠቅሞ በአገራችን የሚታየውን የለውጥ አዝማሚያ ለመቀልበስ ይሠራ ነበር፡፡ በተጨማሪም የለውጥ አመራሮችን የሚያሳቅቁ የእሥርና የግድያ ዛቻዎችንና የደኅንነት ክትትሎችን ያደርግ ነበር፤ የመከላከያ ሠራዊቱን በመጠቀም መፈንቅለ መንግሥት በማድረግ የለውጡን እንቅስቃሴ በወታደራዊ ኃይል ለማፈን ጥረት አድርጎም ነበር፡፡

ከለውጡ በኋላ አዲሱ አመራር በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ስለነበረው በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ታላላቅ የድጋፍ ሰልፎች ተካሂደዋል። ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ማንም ሳይቀሰቅሰው በብዙ ሺዎች የሚቆጠር ህዝብ ለድጋፍ ሰልፍ በወጣበት የመረረ ጥላቻ የነበራቸው አካላት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ለመግደል ሙከራ አድርገዋል። ሙከራው ከከሸፈ በኋላ ነበር የህወሃት ጽንፈኛው ቡድን ወደ መቀሌ በመሰብሰብ የትግራይ ክልልና የፌዴራል መንግሥቱ ግንኙነት የፍጥጫ እንዲሆን መሥራት የጀመረው፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የትግራይ ሕዝብ በፌዴራል መንግስቱ በከፍተኛ ደረጃ እየተጠቃ እንደሆነና ቡድኑ የህዝቡን መብት ለማስጠበቅ እንደሚሰራ በተለያየ መንገድ ፕሮፖጋንዳውን አሰራጭቷል። ይህም ብቻ ሳይሆን የፌዴራል መንግሥቱንና የለውጥ ኃይሉን በሁሉም መስክ ለማዳከምና አጣብቂኝ ውስጥ ለመክተት የተቻለውን ሁሉ አድርጓል። ለአብነት ለመጥቀስ ያህል በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ግጭቶችን በመቀስቀስ ዜጎች እንዲፈናቀሉ ማድረግ፣ ከሀገር ውስጥና ከውጭ አፍራሽ ኃይሎች ጋር አብሮ መሥራት፣ ግድያዎችንና ሽብሮችን ማደራጀትና መምራት፣ የኢኮኖሚ አሻጥር መፈጸም ተጠቃሽ ናቸው።

በህወሃት ጁንታ ቡድን አቀነባባሪነት በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች እንዲሁም በጌዴኦ ዞን ከባድ ግጭቶች እንዲቀሰቀስ በማድረግ የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር በሚሊዮኖች የሚቆጠር እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ። የፌዴሬሽን ምክር ቤት መረጃ እንደሚያመለክተው በአማራ ክልል በሰሜን ጎንደርና በሰሜን ወሎ፣ የቅማንትና የከሚሴ አካባቢ ግጭቶችን በቀጥታና ከጀርባ ሆኖ ደግፏል፡፡ ኦነግ ሸኔን በመጠቀም በደቡብ ክልል ጌዴኦ ዞን በመቶ ሺዎች  የሚቆጠሩ ሰዎች ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ ሲያደርግ በኦሮሚያ ክልል በወለጋ አካባቢ የኦነግ ሸኔ ቡድን በመረጃ፣ በመሣሪያ፣ በሥልጠናና በሰው ኃይል በመርዳት አካባቢው የግጭት ቀጣና ሆኖ እንዲቀጥል አድርጓል። ቡድኑ የተዳፈኑ ግጭቶችን በመቀስቀስና አዳዲስ ግጭቶችን በመፍጠር፣ ዩንቨርሲቲዎችን የግጭት ማእከል እንዲሆኑ በማድረግ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በተደጋጋሚ በንፁሃን ዜጎች ላይ ዘርን መሰረት ያደረገ ጥቃት እንዲደርስ በገንዘብ በመደገፍ ሀገሪቱ እንዳትረጋጋ የለውጡም እሳቤ እንዲደበዝዝ አበክሮ ሰርቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን በመጡ ሰሞን ከፍተኛ ተግዳሮት ከነበሩ ጉዳዮች መካከል የኢኮኖሚ አሻጥር ነበር። የህወሃት ጁንታው ቡድን በኢኮኖሚው መስክ ለረጅም ዓመታት በፈጠረው ትስስር የሀገሪቱን አቅም ፈተና ላይ እንዲወድቅ አድርጎ እንደነበር  ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። የኢኮኖሚ ባለሙያዎችም ይህንኑ አረጋግጠዋል። ለውጡ እንደጀመረ ከፍተኛ የበጀት ጉድለት በማጋጠሙ ለመንግስት ሰራተኞች እንኳ ደመወዝ ለመክፈል አዳጋች እንደበር ተገልጿል። በልማት ስም ከተለያዩ ድርጅቶችና ተቋማት የተወሰደው ብድር ሀገሪቱን ለከፍተኛ የእዳ ጫና ዳርጓት ነበር። ይህም ተጨማሪ ብድር እንዳይገኝ አድርጎ እንደነበር የሚታወስ ነው።

ሌላው የህወሓት ጁንታ ቡድን ኢኮኖሚው እንዲዳከም ያደረገበት መንገድ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ነው፡፡ ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርና የሐሰተኛ የብር ኖት በገበያው ውስጥ በተደጋጋሚ ስለመከሰታቸው በተለያዩ ጊዜያት ሲነገር ቆይቷል። የብሔራዊ ባንክ መረጃ እንደሚያሳየው በኢትዮጵያ እስከ መስከረም 2013 ዓ.ም ከባንክ ሥርዓት ውጪ በገበያ በዝውውር ላይ የነበረው ገንዘብ ከ113 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሶ ነበር፡፡ በህገ ወጥ መንገድ ከባንክ ውጪ ሲንቀሳቀስ የነበረው ገንዘብ የባንኮችን ጥሬ ገንዘብ በእጅጉ እየተፈታተነና እየጎዳ እንደነበር የብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶ/ር ይናገር ደሴ በተደጋጋሚ አስረድተዋል። በተጨማሪም ከባንክ ውጪ ያለው ገንዘብ  ለጤናማ ሥራ ሳይሆን፣ በአብዛኛው ለሕገወጥ ሥራና ለወንጀል በአጠቃላይ ኢኮኖሚውን ለሚጎዱ ጉዳዮች ይውል እንደነበር አዲሱ የብር ኖት ለውጥ በተደረገበት ወቅት ገልጸዋል።

የህወሃት ጁንታ ቡድን ህገ-መንግስታዊ ሂደቱን በተከተለ መንገድ እንዲራዘም የተደረገው ሀገር አቀፍ ምርጫን በመቃወም በህገ ወጥ መንገድ በትግራይ ክልል የምርጫ ኮሚሽን አቋቁሞ ምርጫ አካሂዷል። ቡድኑ ምርጫ መራዘሙን በመቃወም የራሱን ምርጫ ያደረገው ለዴሞክራሲ ባለው ቀናኢነት ሳይሆን በህዝብና በለውጥ ሀይሉ መካከል ተቃርኖንን ለመፍጠር ነው፡፡ በመጨረሻም ህገወጡ የሕወሓት የጥፋት ቡድን ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ምሽት ላይ በክልሉ በሚገኘው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት በማድረስ ክህደት ፈጽሟል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ከፍተኛ የለውጥ ፍላጎት ስለነበራቸው አደባባይ በመውጣት ባሰሙት የተቃውሞ ድምጽ በሀገራችን የመጣው ለውጥ በርካታ ፈተናዎችን ተሻግሯል። የህወሃት ጁንታ ቡድን በህዝብ ግፊነት የመጣው ለውጥ መሰረት እንዳይኖረው ለማድረግ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተለያየ መንገድ የማደናቀፍ ስራ ሲሰራ ቆይቷል።ቡድኑ የለውጡን ሀይል ለማዳከም ነባሩን የአደረጃጀትና ተቋማዊ ሀይል በመጠቀም ስርዓት አለበኝነት እንዲስፋፋ ብዙ ጥረት አድርጓል።

በዚህም በሀገራችን ውስጥ ግድያ፣ መፈናቀል፣ የንብረት ውድመትና የአካል ጉዳት ደርሷል። እነዚህ ሁሉ ተግዳሮቶች ሀገራዊ ለውጡ በተፈለገው ፍጥነት ወደፊት እንዳይንደረደር ጫና ቢያሳድርበትም የህወሃት ጁንታ ቡድን እንዳቀደው ወደኋላ የሚመለስበት ሁኔታ አልተፈጠረም። ይልቁንም ህዝቡ ለውጡን ለማስቀጠል በትዕግስትና በአብሮነት ችግሮቹን ተቋቁሞ በማለፍ ቁርጠኛ መሆኑን አሳይቷል። የጁንታው ቡድንም በመከላከያ ሠራዊቱ ድንቅ ብቃትና ከፍተኛ ቆራጥነት ያሰበው እንዳይሳካ አድርጎታል፤ ህግ የማስከበር ዘመቻውም በአጭር ጊዜ እንዲቋጭ ሆኗል።የዜጎች አብሮነትና መተሳሰብ ረጅም መንገድ ያስኬዳልና ለሀገሪቱ ሁሉን አቀፍ ለውጥ መሳካት የእያንዳንዳችን በጎ አስተዋጽኦ ወሳኝ ነው። ሰላም!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም