ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መዛግብቶችን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት ኤጀንሲ አስረከበ

አዲስ አበባ ታህሳስ 12/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በብሔረሰቦች ጥናት ኢንስቲትዩት የተሰነዱና በምርጫ ቦርድ እጅ የነበሩ የተለያዩ መዛግብቶችን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት ኤጀንሲ አስረከበ።

ከ1960 ዎቹ መጨረሻ እስከ 1980 ዎቹ መጀመሪያ በጹሑፍ፣ በጥናት ጥራዝ፣ በፎቶ ግራፍ፣ በድምፅ ካሴቶችና ሌሎችም የተደራጁም ናቸው።

በተለያዩ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች የተዘጋጁ ሲሆን ፈረንሳይኛና እንግሊዘኛን ጨምሮ በተለያዩ የውጭ አገር ቋንቋዎችም የተዘጋጁ እንደሆኑ ተገልጿል።

የጥናት ጥራዞች፣ ሪፖርቶች፣ ቃለ-ጉባኤዎች፣ መጽሔትና ሌሎች ቅርጾች ያሏቸው ሲሆን ማህበራዊ፣ ምጣኔሃብት፣ የውጭ ግንኙነት ጉዳዮች፣ የህግ ማዕቀፎች፣ ታሪክና ሌሎች ይዘቶችም አሏቸው። 

በተለያዩ አገሮች የተደረጉ ጉብኝቶችና የተወሰዱ ልምዶች ሪፖርት፣ በትጥቅ ትግል ላይ ለነበሩ ኃይሎች የቀረቡ የሰላም ጥሪዎች፣ የድርድር ሂደትን የያዙ መዛግብትም ይገኙባቸዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ በርክክቡ ወቅት እንዳሉት በእውቀታቸው ለአገራቸው አስተዋጽኦ ያደረጉ ምሑራን የሥራ ውጤቶች በአግባቡ ማስቀመጥ ያስፈልጋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ በበኩላቸው መዛግብቶቹ በኢትዮጵያውያን ምሑራን የብሔረሰብ ጥናት ኢንስቲትዩት አማካኝነት የተጻፉና የተሰባሰቡ የመረጃ ሃብቶች ያላቸውን ፋይዳ አስረድተዋል።

እነዚህ የመረጃ ሃብቶች በታሪክ አጋጣሚ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እጅ የነበሩ ሲሆን ለቀጣይ የጥናትና ምርምር ሥራዎች እንዲውሉ መረከባቸውን ጨምረው ገልጸዋል።

በወቅቱ ተሳታፊ የነበሩ አስተያየት ሰጪዎችም የምሑራኑ የሥራ ውጤት ለቀጣይ ጥቅም ላይ ለማዋል ወደ ኤጀንሲው መግባታቸውን በበጎ ጎን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም