ቀጥታ፡

ሁለተኛው የባለ ልዩ ጣዕም የቡና ቅምሻ ውድድር ከየካቲት ወር አጋማሽ ጀምሮ ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ ታህሳስ 12/2013 (ኢዜአ) ሁለተኛው የባለ ልዩ ጣዕም የቡና ቅምሻ ውድድር ከየካቲት ወር አጋማሽ ጀምሮ ሊካሄድ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።

ለውደድሩ አርሶ አደሮች የቡና ናሙናዎቻቸውን እንዲያቀርቡም ጥሪ ተላልፏል፡፡

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ፤ ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ ባካሄደችው የባለ ልዩ ጣዕም የቡና ቅምሻ ውድድር ውጤታማ እንደነበረች ገልፀው ውድድሩ በተለይ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር የሥራ አመራር ቦርድ ፕሬዚዳንት ቅድስት ሙሉጌታ ውድድሩ በቡና ልማት ዘርፍ ላይ እየተሳተፉ ላሉ በሙሉ ክፍት መሆኑንና ከጥር 24 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ የውድድር ናሙናዎችን እንደሚቀበሉ ተናግረዋል፡፡

የተሳታፊዎቹን ናሙና በጅማ፣ ሃዋሳ፣ ድሬዳዋና አዲስ አበባ ለመቀበል ዝግጅት መደረጉንም ጠቁመዋል፡፡

ለዚህ ውድድር አርሶ አደሮች የቡና ናሙናዎቻቸውን እንዲያቀርቡም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር ዋና ሥራ አስኪጅ እና የውድድሩ አስተባባሪ አቶ ግዛት ወርቁ ተወዳዳሪዎቹ በዋናነት የቡና ገበሬዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ቡና ላኪዎች፣ አቅራቢዎች፣ ዩኒየኖች፣ ህብረት ሥራ ማህበራትና ሌሎች ተሳታፊዎች ከአምራች አርሶ አደሩ ጋር ተቀናጅተውና ትስስር ፈጥረው ተሳታፊ እንደሚሆኑ ገልጸዋል።

"በውድድሩ አርሶ አደሩ በታጠበ ቡና ዝቅተኛ 336 ኪሎ ግራም፤ ከፍተኛው ደግሞ 1 ሺህ 722 ኪሎ ግራም በማቅረብ ተሳታፊ መሆን ይኖርበታል" ብለዋል፡፡

በደረቅ ቡና ከሆነ ዝቅተኛው 288 ኪሎ ግራም፤ ከፍተኛው 1ሺህ 476 ማቅረብ እንደሚጠበቅበት አስረድተዋል።

የባለ ልዩ ጣዕም የቡና ቅምሻ ውድድር (ካፕ ኦፍ ኤክሰለንሲ) በኢትዮጵያ ሲዘጋጅ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም