የሰብዓዊ መብቶች ትምህርት በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ እንዲካተት ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
የሰብዓዊ መብቶች ትምህርት በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ እንዲካተት ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 12 ቀን 2013 (ኢዜአ) የወጣቱን ትውልድ የአስተሳሰብና የባህሪ ለውጥ በሚቀያንጽ መልኩ የሰብዓዊ መብቶች ትምህርት በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ እንዲካተት ተጠየቀ።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሰብዓዊ መብቶች ትምህርት አሰጣጥ ላይ ያተኮረ ዐውደ ጥናት ዛሬ አካሂዷል።
በኮሚሽኑ የግንዛቤ ማስፋፊያ ከፍተኛ ባለሙያ ዶክተር ሚዛኔ አባተ በዚህን ወቅት ሰብዓዊ መብቶች ሳይከበሩ የህግ የበላይነት፣ ዴሞክራሲና ዘላቂ ልማትን ማሳካት እንደማይቻል ተናግረዋል።
“በመሆኑም በሥነ-ዜጋና በሥነ-ምግባር ትምህርት ውስጥ ተቀላቅሎ እየተሰጠ ያለው የሰብዓዊ መብቶች ትምህርት በቂ ባለመሆኑ ሥርዓተ ትምህርቱን ማሻሻል ያስፈልጋል” ብለዋል።
በተለይ ለመጀመሪያና ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ስለ ሰብዓዊ መብቶች አከባበር ዕውቀት መጨበጥ እንዳለባቸው አመልክተዋል።
የትምህርቱ መሰጠት ትውልዱ በሰብዓዊ መብቶች እሴቶች ላይ ዕውቀትና ክህሎት በመያዝ አመለካከቱን እንዲቀይር እንደሚያስችልም ነው ዶክተር ሚዛኔ የገለጹት።
ሰብዓዊ መብቶችን የሚያከብርና የሚያስከብር ትውልድ ለመፍጠር ደግሞ ከታችኛው የትምህርት እርከን ጀምሮ የሰብዓዊ መብቶችን መርሆዎችና እሴቶችን ማስረጽ እንደሚገባም አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ በበኩላቸው ትምህርት አሰጣጥን በአግባቡ በመፈተሽ በስነ-ምግባር የታነፁና ህግ አክባሪ ዜጎችን መፍጠር እንደሚገባ ተናግረዋል።
ሥርዓተ ትምህርቱ ህግ አክባሪ፣ የሃሳብ ልዩነቶችን የሚቀበሉ፣ የሴቶችና ህጻናት፣ የአካል ጉዳተኝነት መብቶችን የሚያከብሩ ዜጎች ማፍራት እንደሚጠበቅበትም ገልጸዋል።
ሰብዓዊ መብቶች ትምህርት በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ከተካተተ የአስተሳሰብና የባህሪ ለውጥ እንደሚያመጣም ዶክተር ዳንኤል አስረድተዋል።
ኮሚሽኑ በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ለማካተት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመስራት ላይ እንደሚገኝም አመልክተዋል።