በጋምቤላ ክልል ወንጀሎችን ለመከላከል የጸጥታ መዋቅሩን የማጠናከር ስራ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል ወንጀሎችን ለመከላከል የጸጥታ መዋቅሩን የማጠናከር ስራ እየተከናወነ ነው
ጋምቤላ ታህሳስ 12 /2013 (ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል ህገ ወጥ የጦር መሳሪያን ጨምሮ ሌሎችም ወንጀሎችን ለመከላከል የጸጥታ መዋቅሩን የማጠናከር ስራ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ።
በተለያዩ ምክንያቶች ተቀንሰው የነበሩ ከ450 በላይ የጸጥታ አባላትን ወደ ክልሉ የጸጥታ መዋቅር ለመመለስ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ የተሀድሶ ሥልጠና መስጠት ተጀምሯል።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ኡቶው ኡኮት ሥልጠናውን ሲከፍቱ እንዳሉት በክልሉ ድንበር ዘለል የጸጥታ ችግር፣ ህገ - ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውና ሌሎች ወንጀሎችን ለመከላከል የክልሉን ጸጥታ መዋቅር በሰው ኃይል የማጠናከር ስራ እየተከናወነ ነው ።
በበጋው ወራት በደቡብ ሱዳን የሙርሌ ጎሳ ድንበር በማቋረጥ ህፃናትን አፍኖ የመውሰድና የቀንድ ከብት ዘረፋ ወንጀልን ለመከላከል የክልሉን የሚሊሻ፣ መደበኛ ፖሊስና ልዩ ኃይል አባላትን ማጠናከርም እንዲሁ።
በተለይም ከመደበኛ ፖሊስ፣ ልዩ ኃይል፣ መከላከያና ፌደራል ፖሊስ በተለያዩ ምክንያት የተቀንሰው የቆዩ የጸጥታ አካላትን ወደ ክልሉ ጸጥታ መዋቅሩ እንዲመለሱ በማድረግ መዋቅሮችን የማጠናከር ስራ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።
ወደ ክልሉ የጸጥታ መዋቅር እንዲመለሱ የተደረጉት አባላት በተለይም ክልሉ ሰፊ የድንበር ወሰን ያለው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በዘርፉ የሚታየውን የጸጥታ ኃይል እጥረት እንደሚያቃልሉም ጠቁመዋል።
የክልሉ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ቱት ኮር በበኩላቸው ተመላሽ የጸጥታ አባላት የተሀድሶ ሥልጠናቸውን አጠናቀው ወደ የጸጥታ መዋቅሩ ሲቀላቀሉም ከብሔረተኝነትና ብልሹ አሰራር በጸዳ መልኩ ህዝቡን በታማኝነት እንዲያገለግሉ አሳስበዋል።
ከተመላሾች የጸጥታ አካላት መካከል 150 በመደበኛ ፖሊስ መዋቅር ቀሪዎቹ የልዩ ኃይልን እንደሚቀላቀሉም አስታውቀዋል።
የጸጥታ አባላቱ በአስር ቀን ቆይታቸው በሰብአዊ መብት፣ ወንጀል መከላከልና ሌሎች ርዕሰ ዙሪያ የንድፈ ሃሰብና የተግባር ሥልጠና እንደሚወሰዱ ከወጣው የድርጊት መረሃ ግብሩ ለመረዳት ተችሏል።