ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ተጀመረ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 11/2013 ( ኢዜአ) የ2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ትናንት በተካሄዱ የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎች ተጀምሯል።

የኮቪድ -19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣው ፕሮቶኮል መሰረት የሊጉ ጨዋታዎች በዝግ ሜዳ በባህር ዳር፣ ሃዋሳ እና አዲስ አበባ ከተሞች እንደሚደረጉ የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ማስታወቁ ይታወሳል።

ከታህሳስ 10 እስከ 23 ቀን 2013 ዓ.ም በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም በሚገኘው የእጅ ኳስ ሜዳ የመጀመሪያ አራት ጨዋታዎች ለማካሄድ መርሃ ግብር የወጣ ሲሆን በዚሁ መሰረት የሊጉ ውድድር ትናንት በተካሄዱ የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎች ተጀምሯል።

በፕሪሚየር ሊጉ የመክፈቻ ጨዋታ ጎንደር ከተማ ሚዛን አማን ከተማን 26 ለ 16 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

ትናንት በተደረገ ሌላ የሊጉ ጨዋታ ፌደራል ማረሚያ ቤቶች አዲሱን የፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ ክለብ ባህር ዳር ከተማን 36 ለ 24 ረቷል።

የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ተካሄደዋል።

የ2011 ዓ.ም የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ከምባታ ዱራሜን 27 ለ 19 በማሸነፍ የውድድር ዓመቱን በድል ጀምሯል።

መከላከያና ፌደራል ፖሊስ ባደረጉት ጨዋታ መከላከያ 32 ለ 20 ተጋጣሚውን አሸንፏል።

ቂርቆስ ክፍለ ከተማ የመጀመሪያ ሳምንት የፕሪሚየር ሊግ መርሃ ግብር አራፊ ክለብ ነው።

የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከአንድ ቀን እረፍት በኋላ ታህሳስ 13 እና 14 ቀን 2013 ዓ.ም ይካሄዳሉ።

በተያያዘ ዜና ቡታጅራ ከተማ የእጅ ኳስ ክለብ በፋይናንስ ችግር ምክንያት በፕሪሚየር ሊጉ የማይሳተፍ መሆኑን በማሳወቁ ምክንያት ከውድድሩ ውጪ መሆኑን የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

ሌላኛው የፕሪሚየር ሊጉ ተሳታፊ መቐለ ሰብዓ እንደርታ በትግራይ ክልል ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት በባህር ዳር ሊያደርጋቸው የነበሩ ጨዋታዎች እንደ ተስተካካይ ጨዋታ ተይዘውለት በሃዋሳ በሚካሄደው ውድድር ላይ እንዲሳተፍ ሀሳብ እንደቀረበለት ገልጿል።

መቐለ ሰብአ እንደርታ በክልሉ ከሚገኘው ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በመነጋገር ውሳኔውን ያሳውቃል ተብሎ ይጠበቃል።


በባህር ዳር የሚካሄዱት የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ከተጠናቀቁ በኋላ በሃዋሳ ከተማ ከጥር 8 እስከ 17 ቀን 2013 ዓ.ም የሦስት ሳምንት እንዲሁም ከየካቲት 6 እስከ 15 ቀን 2013 ዓ.ም የሁለት ሳምንት ጨዋታዎች በአዲስ አበባ እንደሚካሄዱ የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

የሁለተኛው ዙር የሊጉ ውድድር በተመሳሳይ እንደ አንደኛ ዙር በእነዚሁ ከተሞች እንደሚከናወን የተገለጸ ሲሆን የዘንድሮው ዓመት ፕሪሚየር ሊግ ሰኔ 30 ቀን 2013 ዓ.ም ለማጠናቀቅ ዕቅድ መያዙ ታውቋል።

በሊጉ ውድድር የሚሳተፉ ተጫዋቾች፣ አሰልጣኞች፣ ዳኞችና ሌሎች በውድድሩ የሚሳተፉ አካላት ምርመራ ተደርጎላቸው ወደ ውድድር መግባታቸውን ነው ፌዴሬሽኑ ያመለከተው።

የ2012 ዓ.ም የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት መቋረጡንና ውድድሩ ያለ አሸናፊ እንዲሰረዝ መደረጉ የሚታወስ ነው።


ካለፈው ዓመት በፊት በተካሄዱ የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ውድድሮች መከላከያ፣ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ እና ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ አሸናፊዎች እንደነበሩ አይዘነጋም።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም