ለኤርትራ ስደተኞች የሚቀርበው የሰብዓዊ እርዳታ እንደገና ተጀምሯል -የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ - ኢዜአ አማርኛ
ለኤርትራ ስደተኞች የሚቀርበው የሰብዓዊ እርዳታ እንደገና ተጀምሯል -የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ
ባህር ዳር፣ ታህሳስ 11/2013(ኢዜአ ) በትግራይ ክልል ሲካሔድ ከቆየው የህግ ማስከበር ስራ ጋር ተያይዞ ለኤርትራ ስደተኞች ተቋርጦ የነበረው ሰብአዊ እርዳታ እንደገና መከፋፈል መጀመሩን የኢትዮጵያ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ አስታወቀ።
የምግብ አቅርቦቱ ወቅታዊ ችግሮቻችንን አቃሎልናል ሲሉ ስደተኞች ተናግረዋል።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ ለኢዜአ እንደገለፁት ኢትዮጵያ ከተለያዩ 26 ሃገራት የመጡ ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ስደተኞችን ተቀብላ እያስተናገደች ትገኛለች።
ስደተኞቹ በአብዛኛው ከደቡብ ሱዳን፣ ሱዳንና ኤርትራ፣ ሶማሊያና ሌሎች ሃገራት የመጡ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በአምስት ማስተባበሪያዎች ዞኖች ውስጥ በሚገኙ 26 ስደተኛ ማስተባበሪያ ጣቢያዎች አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ ነው።
ኢትዮጵያ ለስደተኞቹ የምግብ፣ የጤና፣ የህግ ከለላ፣ የትምህርትና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶችን በተሟላ መንገድ በመስጠት አለም አቀፍ ግዴታዋን እየተወጣች መሆኑን ገልፀዋል።
ይሁን እንጅ በትግራይ ክልል በተፈጠረው ወቅታዊ ሁኔታና መንግስት እየወሰደ ባለው የህግ ማስክበር እንቅስቃሴ ለኤርትራ ስደተኞች ይቀርብ የነበረው የምግብ አቅርቦት ለተወሰነ ጊዜ ተቋርጦ መቆየቱን አስታውሰዋል።
በትግራይ ክልል 100 ሺህ የሚሆኑ የኤርትራ ስደተኞች እንደሚኖሩ ጠቅሰው፤ ስደተኞቹ በካምፕ ውስጥና ከካምፕ ውጭ እንደሚኖሩ ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።
በማይ አይኒ፣ አዲሐሩሽ፣ ሽመለባና ህፃፅ የመጠለያ ካምፖች ከ46 ሺህ የሚበልጡ ስደተኞች የሚኖሩ ሲሆን አካባቢው በተረጋጋባቸው ማይ አይኒና አዲ ሐሩሽ ካምፖች የምግብ እደላ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ መጀመሩን አብራርተዋል።
“በአሁኑ ወቅት 28 መኪና የስንዴ፣ በቆሎ፣ የአልሚ ምግብ፣ ዘይት፣ ክክና ሌሎች የምግብ እህል መቅረቡን ጠቅሰው፤ እስከ አሁንም 18 መኪና እህል ተጓጉዞ ለተጠቃሚዎች እየተከፋፈለ ይገኛል” ብለዋል።
አቅርቦቱ በተጠናከረ ሁኔታ እንደሚቀጥል አመልክተው ሌሎች በስደተኞች ዙሪያ የሚሰሩ ድርጅቶችም የአካባቢውን መረጋጋት በማየት ተመልሰው ወደ ስራ መግባታቸውን ገልፀዋል።
በችግሩ ወቅት በተፈጠረ መደናገጥ የተወሰኑ ስደተኞች ከካምፕ ወጥተው ወደ ተለያዩ ከተሞች ገብተው እንደነበር አስታውሰው፤ “እስከ አሁን በተሰራ ስራም ከአዲስ አበባ ከ600 በላይ ስደተኞች ወደ ካምፕ እንዲገቡ ተደርጓል”ብለዋል።
ቀሪዎቹ የአካባቢውን መረጋጋት በማረጋገጥ የመመለሱ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
ተጠናክሮ የቀጠለው ሰብዓዊ እርዳታውን የማከፋፈል ስራ እንዳለ ሆኖ የውሃ፣ የመብራትና ሌሎች አገልግሎቶች ፈጥነው አገልግሎት እንዲሰጡም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በኤጀንሲው የወቅታዊ ችግር ምላሽ ሰጭ ቡድን አባል አቶ ሙሉቀን ጥላሁን ናቸው።
በወቅታዊ ችግሩ ተደናግጠው የወጡ ስደተኞች በተቀናጀ አግባብ የመመለስ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ በካምፖች እየተሰጠ ያለው መደበኛ አገልግሎት በመጀመሩም ፈጥነው እንዲመለሱም አሳስበዋል።
በአካባቢው ተፈጥሮ የነበረው ወቅታዊ ችግር በስደተኞች ላይ ከፍተኛ መደናገጥ ፈጥሮ ነበር ያለው በስደተኞች ካምፕ ለ10 ዓመታት ያህል የቆየው ወጣት ሃብቶም ሃይሌ ነው።
የውሃ፣ የምግብና ሌሎች አገልግሎቶች በመቋረጣቸው ምክንያት ለችግር በመጋለጣቸው የተወሰኑ ስደተኞች በፍርሃት የተነሳ ካምፑን ለቀው መውጣታቸውን ገልጿል።
አሁን ላይ አካባቢው ወደ ቀደመ ሰላሙ በመመለሱ ማይፀብሪና አዲአርቃይ ድረስ በመሄድ ገበያ መገብየት መጀመራቸውን ተናግሯል።
የምግብ አቅርቦትና ሌሎች እደላዎች መጀመራቸውም ከነበረባቸው ችግር እንዳላቀቃቸው ጠቅሶ ካምፑን የለቀቁ ስደተኞችም አሁን ላይ የቀደመ አገልግሎቱ በመመለሱ ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ ጥሪውን አስተላልፏል።
ሌላኛዋ የኤርትራ ስደተኛ ወይዘሮ ሄለን አፅበሃ በበኩላቸው ተፈጥሮ በነበረው የፀጥታ ችግር ሦስት ልጆቻቸውን ጨምሮ ከፍተኛ መደናገጥ ውስጥ ወድቀው እንደነበረ ተናግረዋል።
በተለይም ችግሩ ሳይታሰብ የተፈጠረ በመሆኑና የገንዘብም ሆነ የምግብ እህል ባለመኖሩ ለከፋ ችግር ተጋልጠው እንደነበረ ገልፀዋል።
አሁን ላይ አካባቢው ወደ ሰላማዊ ሁኔታ መመለሱና የምግብ አቅርቦት ችግሩ መፈታቱ እንዳስደሰታቸው አመልክተው በቀጣይም የመብራትና የውሃ አገልግሎት እንዲጀመር ጠይቀዋል።
በወቅታዊ ችግር ተደናግጠው ከጣቢያ የወጡ ስደተኞችም አሁን ላይ ሁኔታው በመረጋጋቱ የምግብ አቅርቦት የተጀመረ መሆኑን ተረድተው ወደ ቀደመው መኖሪያ ጣቢያቸው መመለስ እንደሚችሉ ገልጻለች።