ቀጥታ፡

የቦክስ ተወዳዳሪዋ በዓለም የወጣቶች ኦሎምፒክ ላይ ለመካፈል የሚያስችላትን ድል አስመዘገበች

አዲስ አበባ ግንቦት 1/2010 በአፍሪካ ወጣቶች ቦክስ ውድድር የተካፈለችው ሀና ደረጀ በዓለም የወጣቶች ኦሎምፒክ ለመካፈል የሚያስችላትን ድል አስመዝግባለች። በሞሮኮ እየተካሄደ ባለው  የአፍሪካ ወጣቶች ቦክስ ውድድር ኢትዮጵያን ወክላ የተሳተፈችው ሀና ደረጀ  ለፍጻሜ ደርሳለች። በዚህ የአፍሪካ ወጣቶች የቦክስ ውድድር በሴቶች ኢትዮጵያን ወክላ በብቸኝነት የተካፈለችው ሀና ከ45 እስከ 48 ኪሎ ግራም በተደረገ ውድድር ነው የአልጀሪያ ተጋጣሚዋን በማሸነፍ ቅዳሜ ለሚደረገው የፍጻሜ ውድደር ማለፏን ያረጋገጠችው ። በዚህ የአፍሪካ ወጣቶች ቦክስ ውድድር ላይ የወርቅና የብር ሜዳሊያ ያመጡ ቦክሰኞች አገራቸውን ወክለው በዓለም ወጣቶች ኦሎምፒክ ውድድር ላይ ይካፈላሉ። ይህን ተከትሎም ሀና ደረጀ በፍጻሜው ውድድር አሸናፊ ብትሆንም ባትሆንም በጥቅምት ወር 2011 ዓ.ም በአርጀንቲና ርዕሰ መዲና ቦነስ አይረስ በሚካሄደው የዓለም ወጣቶች ኦሎምፒክ  ውድድር ተካፋይ መሆኗን አረጋግጣለች። ሀና ደረጀ የኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ ያፈራት ተወዳዳሪ ናት። ኢትዮጵያ በዚህ የአፍሪካ የወጣቶች ውድድር ላይ የሚካፈሉ ሌሎች አራት ተወዳዳሪዎች ያሏት ሲሆን በ52 ኪሎ ግራም ፍቅረ ማርያም ያደሳ እና በ56 ኪሎ ግራም ቢላል አስራት በተጋጣሚዎቻቸው ተሸንፈው ከውድድሩ ውጭ ሆነዋል። ሌሎች ኢትዮጵያን የወከሉት ተመስገን ምትኩ ዛሬ በ64 ኪሎ ግራም የሚጫወት ሲሆን ነገ በ49 ኪሎ ግራም እንዳሻው አላዩ ውድድሩን የሚያደርግ ይሆናል። በሞሮኮ እየተካሄደ የሚገኘው ይህ ውድድር ከሚያዚያ 27 ቀን ጀምሮ እየተከናወነ ሲሆን ግንቦት 5 ቀን 2010 ዓ.ም ፍጻሜውን ያገኛል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም