በአሜሪካ ከሚኖሩ ዳያስፖራዎች በኢትዮጵያ ለኮቪድ-19 መከላከያ የሚውል ከ1 ሚሊዮን ዶላር በላይ መሰብሰቡ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በአሜሪካ ከሚኖሩ ዳያስፖራዎች በኢትዮጵያ ለኮቪድ-19 መከላከያ የሚውል ከ1 ሚሊዮን ዶላር በላይ መሰብሰቡ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 11/2013 ( ኢዜአ) በአሜሪካ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ለሚሰሩ ሥራዎች የሚውል ከ1 ሚሊዮን ዶላር በላይ መሰብሰቡን በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ ገለጹ።
በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተያዘ የመጀመሪያው ሰው መጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም ከተመዘገበበት ጊዜ አንስቶ ወረርሽኙ በስፋት እየተዛመተ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
በአገሪቱ የወረርሽኙን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየተከናወኑ ላሉ ሥራዎች በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ድጋፍ እያደረጉ መሆኑም ይታወቃል።
በአሜሪካ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንም የወረርሽኙን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየተሰሩ ላሉ ስራዎች እስካሁን ከ1 ሚሊዮን ዶላር በላይ በገንዘብና በአይነት ድጋፍ ተሰብስቧል።
በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ በፌስቡክ ገጻቸው ባሳፈሩት ጽሁፍ እንዳስታወቁት በአሜሪካ ልገሳ ባደረገው ሰው ብዛትም ሆነ በተደረገው የገንዘብ ድጋፍ አዲስ ከብረወሰን ማስመዝገብ ተችሏል።
በአሜሪካ የሚኖሩ ከ1 ሺህ 500 በላይ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ከ1 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለግሰዋል።
ኢትዮጵያ ወረርሽኙ ያሳደረባትን ጫና ለመቋቋም እንዲያግዝ ኢትዮጵያዊያኑ በህብረት ሆነው ላደረጉት ድጋፍም አምባሳደሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
"በኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከልና መቆጣጠር ላይ የታየው ትብብር በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እምነቴ ነው" ብለዋል አምባሳደር ፍጹም።
በተለያዩ አገራት የሚገኙ የዳያስፖራው ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ኮቪድ-19ን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ለሚሰሩ ሥራዎች ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የገንዘብና የአይነት ድጋፍ ማድረጋቸውን ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።