የፖሊሳዊ ሙያ ተቀባይነትን የሚያሳድጉ ስራዎች ይከናወናሉ...የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ - ኢዜአ አማርኛ
የፖሊሳዊ ሙያ ተቀባይነትን የሚያሳድጉ ስራዎች ይከናወናሉ...የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ
አዲስ አበባ ታህሳስ 9/2013 (ኢዜአ) የፖሊሳዊ ሙያን በማሳደግ አሰለጣጠኑን ማዘመን የዘርፉን አገልግሎት ይበልጥ እንደሚያሳድግ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነርና የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፕሬዝዳንት መስፍን አበበ ገለጹ።
የፖሊስ ሙያ ትምህርትና ስልጠናን የደረጃ ምዘና ለመስጠት በተዘጋጀው ሰነድ ዙሪያ ሰንዳፋ በሚገኘው የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ለሁለት ቀናት የምክክር መድረክ ተካሂዷል።
በዚህ ወቅት ኮሚሽነር መስፍን አበበ የሰነዱ አላማ ቀደም ሲል በሃገራችን የነበረው የፖሊስ ትምህርትና ስልጠና ከሌሎች የሙያ ዘርፎች እኩል ተወዳዳሪ ባለመሆኑ ሰነዱ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።
“የፖሊስ ልዩ ባህሪንና ተልእኮን መሰረት ያደረገ እንደ ፖሊስ ሊሰራ የሚገባውን የእውቀት፣ የክህሎት በተለይም ከሌሎች ሙያዎች የሚለዩት ስብእናን ጭምር አጣጥሞ የያዘ ዘመናዊና የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ነው” ብለዋል።
ሰነዱ በሀገሪቱ በፖሊስ ሙያ ላይ ያሉ ባለሙያዎች ተመሳሳይ የሙያ ብቃት፤ ክህሎት እንዲሁም እውቀት ያላቸውና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚያስችላቸው መሆኑንም ገልጸዋል።
ምክትል ኮሚሽነሩ አክለውም ሰነዱ ከፖሊስ ሙያ ትምህርትና ስልጠና የሚመረቁ የፖሊስ አባላት በተመረቁበት ሙያ በማገልገል ተቀባይነት እንዲኖራቸው፤ ተገቢውን ጥቅማጥቅም እንዲያገኙ ግዴታና ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የሚያደርግ መሆኑንም አስረድተዋል።
ኮሚሽነሩ የፖሊስ አባላት ለረጅም ጊዜ ሲጠይቁት የነበረ ጥያቄ ተመልሷል፤ ለተግባራዊነቱም እንሰራለን ብለዋል።
“ሰነዱ በጣም አስፈላጊና እንደ ሀገር የሚጠቅም ነው” ሲሉም ምክትል ኮሚሽነር አበበ አረጋግጠዋል።
በሰነዱ ዝግጅት በዋናነት ተሳታፊ የነበሩት የኦሮሚያ ፖሊስ ኮለጅ መምህር ቺፍ ኢንስፔክተር ሀብታሙ ጉደታ እስከ አሁን በነበረው የፖሊስ አባላት ስልጠናም ሆነ ምልመላ አሰራር ላይ ወጥ መስፈርት አለመኖሩን ገልጸዋል።
ይህ አካሄድ ደግሞ በፖሊስ አባላቱ ላይም ሆነ በሀገሪቱ ላይ የአሰለጣጠንና የአሰራር ችግር መፍጠሩን አመልክተዋል።
ኢንስፔክተሩ እንዳሉት የተዘጋጀው አዲሱ ሰነድ በሙያ አይነት ተከፋፍሎ የስልጠና ድግግሞሽን በማስቀረት፡ ጊዜና ሀብትን በመቀነስ ባለሙያው በቂ እውቀት ይዞ እንዲወጣ ያደርጋል።
ሰነዱ በፍኖተ ካርታ የታቀፈ ዘመናዊ በመሆኑ ሀገሪቱ የምትፈልገውን አገልግልት በመስጠት ረገድ ሰፊ ጥቅም ይሰጣል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የፖሊስ ሳይንስ መምህር ምክትል እንስፔክተር ልኬ የኔሁን በበኩላቸው “ጥናቱ ወጥ በሆነ ስታንዳርድ ፖሊስ ሀገር አቀፋዊ እውቀት እንዲኖረው የሚያስችል ነው” ብለዋል።
የተዘጋጀው ጥናት ፖሊስ በሙያዊ እውቀት የተካነ በመሆን ለሀገሪቱ የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጥና ለግሉም የተሻለ ተጠቃሚ የሚሆንበትን እድል የሚያመቻች መሆኑን አስረድተዋል።
የፖሊስ ሙያ ትምህርትና ስልጠናን የደረጃ ምዘና ለመስጠት የተዘጋጀውን ሰነድ የኦሮሚያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅና የፌደራል ፖሊስ ትምህርት ሙያና ስልጠና ተቋም በጋራ እንዳዘጋጁት ተመልክቷል።
በአዲሱ ሰነድ የሚሰጠው ትምህርትና ስልጠና የፖሊስ አባላቱን ከሌሎች ሙያ ዘርፎች እኩል ተወዳዳሪ የሚያደርግ እንደሆነም ተገልጿል።