ለአዳማ ከተማ አዲስ መዋቅራዊ ፕላን ተዘጋጀ

105
አዳማ ሀምሌ 13/2010 የአዳማ ከተማን ልማት ለማፋጠንና እድገቷን ለማዘመን የሚያስችል አዲስ መዋቅራዊ ፕላን ተዘጋጀ። አዲሱ የአዳማ ከተማ መዋቅራዊ ፕላን የርክክብ ስነስርዓት ወቅት በልማቱ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ግለሰቦችና ድርጅቶች ትናንት እውቅና ተሰጥቷል። የቀድሞ የአዳማ ከተማ ከንቲባና የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ አዳነች ሀቤቤ በዚህ ወቅት እንደገለጹት አዲሱ መዋቅራዊ ፕላን የከተማዋን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ለማፋጠንና እድገቷን ለማዘመን ወሳኝ ነው፡፡ " ፕላኑ የከተማዋን የቀጣዩን አስር ዓመታት ሁሉን አቀፍ የእድገት ጉዞን በዝርዝር ያመላከተ ከመሆኑንም ባሻገር የህዝቡን ባህል፣ታሪክና የአኗኗር ዜይቤ ከግምት ውስጥ ያሰገባ ነው "ብለዋል። ፕላኑን ለማዘጋጀት የተለያዩ መስኮችን የዳሰሱ ጥናቶች መካሄዳቸውን ያመለከቱት ወይዘሮ አዳነች በዋናነት የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም፣የመልካም አስተዳደር፣የህዝቡ ባህልና ታሪክን ጨምሮ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ዘርፎች ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ በፕላኑ ዝግጅት በየደረጃው የሚገኙ ሙያተኞችን፣ የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ፣የኦሮሚያ ከተሞች ፕላን ኢንስቲትዩት ምሁራን የተሳተፉበትና ዓለም አቀፍ  ተሞክሮን መሰረት ያደረገ መሆኑንም አመልክተዋል። "አዲሱ መዋቅራዊ ፕላን የከተማዋን የኮንፈረንስ፣ኢንዱስትሪና የቱሪዝም ማዕከልነቷን ይበልጥ የሚያረገግጥ ከመሆኑም ባለፈ ለዕድገቷ መፋጠን ፋይዳው የላቀ ነው" ብለዋል። ከተማዋ ዘመናዊና ሰው ሰራሽ የውሃ አካላት በመዋቅራዊ ፕላን እንደሚኖር ጠቁመው ለፕላኑ ተግባራዊነትና ውጤታማነት ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ አዲስ የተዘጋጀው መዋቅራዊ ፕላን አሁን በከተማዋ የሚታየውን የመሬት ወረራ፣ ህገ ወጥ ግንባታና  በዘርፉ የሚስተዋለውን ኪራይ ሰብሳቢነትን  ለማስወገድ ቁልፍ መሳሪያ መሆኑን የገለጹት ደግሞ አዲሱ የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ መስፍን አሰፋ ናቸው። " ፕላኑ የከተማዋን ልማትና ዕድገት ለማዘመን ብቸኛ አማራጭ ነው " ያሉት ከንቲባው በአሁኑ ወቅት ህብረተሰቡ ለሚያነሳቸው  የልማት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ጭምር አጋዥ  መሆኑን ተናግረዋል። ከከተማዋ ነዋሪዎች ባለፈ የአካባቢውን አርሶ አደሮች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ዝርዝር ጉዳዮችን የያዘ መሆኑንም አመልክተዋል። አዲሱ መዋቅራዊ መስተር ፕላን ከተማዋ አሁን የደረሰችበትን ሁሉን አቀፍ ልማትና እድገት  ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር ያስችላል። በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩት ባለሃብት አቶ አንዋር ሰይድ በሰጡት አስተያየት መዋቅራዊ ፕላኑ የከተማዋን እድገት ለማፋጠን  ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ለተግባራዊነቱ በሙያቸው እንደሚያግዙም ጠቁመዋል። የአንድ ከተማ ልማትና  እድገት የሚወሰነው አግባብነት ያለው ዘመናዊ ማስተር ፕላን ሲኖረው መሆኑን የገለጹት ደግሞ  ባለሀብት የሆኑት ኢንጅነር ዲርባ ደፈርሳ ናቸው። የከተማዋ መሰረተ ልማት ዓለም አቀፍ ደረጃን ጠብቀው እንዲካሄዱ  አዲሱ መዋቅራዊ ፕላን ድርሻው የላቀ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ አዲሱ መዋቅራዊ ፕላን ለአዳማ ከተማ አስተዳደር ያስረከበው የኦሮሚያ ከተሞች ፕላን ኢንስቲትዩት ነው፡፡ የአዳማ ከተማን ልማት እድገት ለማፋጠን በተደረገው ጥረት የላቀ አስተዋጽኦ የነበራቸው ባለሃብቶች፣ምሁራንና ድርጅቶች ዋንጫና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም