ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ውድድር ተጀመረ

ባህርዳር ታህሳስ 10/2013 (ኢዜአ) አምስተኛው የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ውድድር ዛሬ በባህርዳር ከተማ ተጀመረ።

ውድድሩ  ከዛሬ ጀምሮ  እስከ ታህሳስ 23/2013ዓ.ም. እንደሚቆይ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍትህ  ወልደሰንበት ውድድሩን  ባስጀመሩበት ወቅት እንደተናገሩት፤በኮሮና ወረርሺኝ ምክንያት የእጅ ኳስ ውድድርም እንደሌሎች የስፖርት ዘርፎች ሁሉ ተቋርጠው ቆይቷል።

የኮሮናን እየተከላከሉ ውድድር ማካሄድ የሚያስችል  የፕሮቶኮል እቅድ በማዘጋጀት  ወደ  ስራ እንዲገባ ፌደሬሽኑ ባደረገው ዝግጅት መሰረት አሰር  ክለቦች የሚሳተፉበት አምስተኛውን ሀገር አቀፍ የእጅ ኳስ ውድድር በባህርዳር ከተማ መጀመር መቻሉን አስረድተዋል።

የአማራ ክልል ስፖርት ምክትል ኮሚሽነር አቶ አዱኛው ይግዛው በበኩላቸው፤ የውድድሩ ዓላማ በህዝቦች መካከል መፈቃቀርንና ወንድም አማማችነትን በመፍጠር ጠንካራ ሀገራዊ አንድነት ለመገንባት በሚደረገው ርብርብ የራስን አሻራ ለማሳረፍ መሆኑን ገልጸዋል።

የስፖርት ዘርፉ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ  ጥቅም የሚኖረውን  ፋይዳ  በመገንዘብ  ህዝባዊ መሰረት ይዞ እንዲያድግ ሁሉም አካል ሊረባረብ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የባህርዳር ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ባዬ አለባቸው  ፤ የባህርዳር ከተማ የዘመናዊ የእጅ ኳስ መወዳደሪያ ሜዳ ባለቤት እንድትሆን ለተባበሩ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

የሜዳው መገንባትም የስፖርት አመራሩ፣ ባለሙያውና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እንዲሁም  የፈረሱ ክለቦች እንደገና እንዲቋቋሙ ተነሳሽነት በመፍጠሩ ውድድሩን በባህርዳር እንዲካሄድ አስችሏል ብለዋል።

የዘንድሮውን የእጅ ኳስ ውድድር ለየት የሚያደርገውም  በዘርፉ ክለብ ያልነበረው የባህርዳር ከተማ እንደ አዲስ አዋቅሮ በውድድሩ ለመሳተፍ መዘጋጀቱ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ለውድድሩ የመጡ የክለብ ስፖርተኞችም በባህርዳር ከተማ የሚኖራቸው ቆይታ አስደሳች እንዲሆን የከተማ አስተዳደሩ ከጎናቸው መሆኑን አስታውቀዋል።

ዛሬ  በመጀመሪያው ፋሲል ከነማ የእጅ ኳስ ክለብ ከሚዛን አማን አቻው ጋር ሲጋጠሙ፤ ቀጥሎም የባህርዳር ከተማ የእጅ ኳስ ክለብ ከፌደራል ማረሚያ ቤቶች እንደሚጫወቱ ከወጣው መረሃ ግብር ማወቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም