ቀጥታ፡

በኢትዮጵያና ኤርትራ የንግድ ትስስር ለመፍጠር ይሰራል

አዲስ አበባ ሀምሌ 13/2010 የኢትዮጵያና ኤርትራ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች በአገራቱ መካከል ምቹ የንግድ ትስስር ለመፍጠር በጋራ እንደሚሰሩ ገለጹ። ምክር ቤቶቹ በአገራቱ የንግድና ኢንቨስትመንት ዕድሎች ላይ የሚመከር የኢትዮ-ኤርትራ የንግድ ፎረም ለመጀመሪያ ጊዜ በአስመራ አካሂደዋል። መድረኩ በሁለቱ አገራት የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ዕድሎች በመለየት ኢኮኖሚያዊ ትስስርን ለመፍጠር ያለመ ነው። የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አሰፋ ገብረዮሐንስ እንደገለጹት የሁለቱ አገራት የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት በጋራ በመስራት በምሥራቅ አፍሪካ አርአያ የመሆን ጊዜያቸው አሁን ነው። ለዚህም ኢትዮጵያዊያን የንግዱ ማኅበረሰብ  በቱሪዝም፣ በገቢና ወጪ ንግድ በኤርትራ ወደቦች ለመጠቀም ፍላጎትና ዝግጁነት አለ። በኤርትራም በኩል የንግድና ኢንቨስትመንት ፖሊሲን ጨምሮ ለኢኮኖሚያዊ ትስስሩ የሚረዱ ምቹ ሁኔታዎች እንዲደረግ አቶ አሰፋ ጠይቀዋል። የኤርትራ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታደሰ ወልደዮሐንስ በበኩላቸው በኢትዮጵያ የንግድ ማኅበረሰብ አባላት የተነሱ ጥያቄዎችን መንግሥት ተቀብሎ ተገቢው ምላሽ ይሰጣል ብለዋል። የሁለቱን አገራት ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት የተቀላጠፈ ለማድረግ ማኅበራቱ በቅንጅት መስራት ይገባቸዋል ሲሉም አክለዋል። ኢትዮጵያና ኤርትራ የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ አባል መሆናቸውም ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቱን ለማጠናከር መልካም አጋጣሚ መሆኑን ጠቁመዋል። በፎረሙ በሁለቱ ወገኖች በኩል ማብራሪያ ያስፈልጋቸዋል የተባሉ ጉዳዮች ተነስተው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን በተለይም የኢትዮጵያና ኤርትራ ኤምባሲዎች የንግድ ትስስርን ለማሳለጥ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ ኃላፊው አመልክተዋል። ኤርትራ በኮሜሳ አባል አገርነቷ ምክንያት በምታስገባቸው ምርቶች ላይ 80 በመቶ የታሪፍ ቅናሽ ማድረጓን በማሳያነት አንስተዋል። ፎረሙን ያዘጋጀው የዋፋ ፕሮሞሽንና ማርኬቲንግ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ፋንታዬ ጌታነህ ፎረሙ ለኢትዮጵያና ኤርትራ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት በር ከፋች መሆኑን ተናግረዋል። በመጪው ጥቅምት 2011 ዓም በእንግሊዝ ለንደን በሚካሄደው የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም ላይም ኤርትራ እንድትሳተፍ ግብዣ አቅርበዋል። ከሁለት አሥርት ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አስመራ ባደረገው በረራ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት መካተታቸው ይታወቃል።                    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም