የአማራ ክልልን የማዕድን ሀብት ፀጋዎች ለማልማት ጥረት እየተደረገ ነው

239

ባሀርዳር ታህሳስ 9/2013 (ኢዜአ) በአማራ ክልል የሚገኙ ዘረፈ ብዙ የማዕድን ሀብት ፀጋዎችን አልምቶ ለመጠቀም ጥረት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ የማዕድን ሃበት ልማት ማስፋፊያ ኤጀንሲ ገለጸ።

በክልሉ የማዕድን ዘርፉን አልምቶ ለመጠቀም የሚያግዝ የአቅም ግንባታ ሥልጠና ለዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች ተሰጥቷል።

የኤጀንሲው ዳይሬክተር አቶ ሃይሌ አበበ  በሥልጠናው ማጠናቀቂያ መድረክ እንዳሉት ክልሉ የበርካታ የማዕድን ሀብት ጸጋዎች ባለቤት እንደሆነ  በጥናት ተረጋግጧል።

በአዊና ዋግ ኽምራ ዞኖች የወርቅ፣  የጅብሰም፣ በሰሜን ሸዋ የብርጭቆና የመስታወት፣ በደቡብ ወሎና ሰሜን ወሎ ኦፓልና ብረት ማዕድናት ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።

እነዚህን ፀጋዎችን ለማልማት በተደረገ ጥረት  በሲሚንቶ ፋብሪካ ግንባታ  ብቻ ስድስት  ባለሃብቶች ፈቃድ ጠይቀው የተሰጣቸውና በሂደት ላይ ያሉም እንደሚገኙ አመልክተዋል።

ኤጀንሲው ከሌሎችም ተቋማት ጋር በመተባበር ተጨማሪ የማዕድን ሃብቶች ዓይነትና  ክምችት ለይቶ በመከለል ለባለሃብት ለማስረከብ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

ለአመራሮችና ባለሙያዎች የተሰጠው ስልጠናም የማዕድን ዘርፉን ለስራ እድል ፈጠራ፣ ለውጭ ምንዛሬ ግኝትና ለገቢ ማስገኛ በማዋል የክልሉ እድገት ለማፋጠን  መሆኑን አስረድተዋል።

የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሃላፊ አቶ ግርማ የሽጥላ  በበኩላቸው   ባለፉት 27 ዓመታት የአማራ ክልል የግብዓት አቅራቢ እንጂ ለኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ተመራጭ እንዳይሆን ታቅዶ ሲሰራ መቆየቱን  አውስተዋል።

በክልሉ የሚገኙ የማዕድን ሀብት ጸጋዎችን በማጥናት፣ የክምችት  መጠናቸውን  በመለየትና  ወደ ልማት በማስገባት ህብረተሰቡን  ተጠቃሚ ለማድረግ  እንዳይቻል  በአሰራር የተደገፈ ሴራ ተፈጽሟል ብለዋል።

አሁን ላይ በመጣው ሀገራዊ ለውጥ የተፈጠረው ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የማዕድን ዘርፉ በማልማት የክልሉ እድገት ለማፋጠንና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ  ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ እንደሆነ ተናግረዋል።

ቢሮውም ባዘጋጀው የኢንዱስትይሪና ኢንቨስትመንት ፍኖተ ካርታ  ለማዕድን ዘርፍ ልማት ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመው በዚህም ባለሃብቶችን፣ የተደራጁ ወጣቶችና ሌሎችን ያሳተፈ ስራ ይሰራል ብለዋል።

በሰሜን ሸዋ ዞን የማዕድን ስራዎች፣ ፈቃድና አስተዳደር ቡድን መሪ አቶ ዘሪሁን ሳህለ በሰጡት አስተያየት በዞኑ ከሚገኙ ማዕድኖች ውስጥ ለሲሚንቶ ፣ ለጅብሰም፣ ብርጭቆና መስታወት ስራ የሚውሉ ማዕድናት እንደሚገኙ ገልጸዋል።

የማዕድን ልማት ለሥራ ዕድል ፈጠራ አዋጭ መሆኑን በዘርፉ የተሰማራ  አንድ የቻይና ኩባንያ  ብቻ ከ500 ለሚበልጡ ሰዎች  የስራ እድል ፈጥሮ አሳይቶናል ብለዋል።

ማዕድን  እስካሁን የተረሳ የኢኮኖሚ ዘርፍ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በዋግ  ኽምራ  ብሔረሰብ አስተዳደር የማዕድን ስራዎች ፈቃድና አስተዳደር ቡድን መሪ አቶ በላይነህ የኔሰው ናቸው።

ሰሞኑን የተሰጠን ስልጠና አቅማችን ከመገንባት ባሻገር በዘርፉ ያሉ መልካም አጋጣሚዎችንና ለችግሮች የመፍትሄ አማራጮችን በመለየት በቁርጠኝነት  ወደ ስራ  በመግባት  ለውጥ ለማምጣት ተነሳሽነትን ፈጥሮልናል ብለዋል።

በወረታ ከተማ ለሶሰት ተከታታይ ቀናት በተሰጠው ሥልጠና ከምዕራብ አማራ የተወጣጡ   ከ220 በላይ የዘርፉ  አመራሮችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም