ኢትዮጵያ ተግባራዊ በሚሆነው የአፍሪካ ሀገራት ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት ተሳታፊና ተጠቃሚ እንድትሆን እየተሰራ መሆኑ ተነገረ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ተግባራዊ በሚሆነው የአፍሪካ ሀገራት ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት ተሳታፊና ተጠቃሚ እንድትሆን እየተሰራ መሆኑ ተነገረ
አዳማ ታህሳስ 9/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ከመጪው ጥር ወር ጀምሮ ተግባራዊ በሚሆነውን የአፍሪካ ሀገራት ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት ተሳታፊና ተጠቃሚ እንድትሆን እየተሰራ መሆኑን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በንግድ ስርዓት ማሻሻያ፣ በአፍርካ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት አተገባበርና ኢትዮጵያን የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለማድረግ እየተከናወኑ ባሉ ስራዎች ዙሪያ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የተዘጋጀ የግንዛቤ መፍጠሪያ መድረክ በአዳማ እየተካሄደ ነው ።
በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የዘርፈ ብዙ ንግድ ግንኙነትና ድርድር ዳይሬክተር አቶ ሙሴ ምንዳዬ ለኢዜአ እንደገለጹት የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት ከመጪ ጥር 2013 ዓም ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል።
ኢትዮጵያ በመርህ ደረጃ የነበረውን የነፃ የንግድ ቀጠና ድርድር በማጠናቀቅ፣ የድርጊት መርሃ ግብር በማውጣትና ወደ ትግበራ ለመግባት የራሷን ዝግጅት በማጠናቀቅ ላይ መሆኗን ተናግረዋል።
በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ስምምነቱን መፈራማቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ ኢትዮጵያን ጨምሮ 34 ሀገራት ስምምነቱን በፓርላማቸው ማጽደቃቸውን ገልጸዋል።
ስምምነቱ ከመጪው ጥር ወር ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንደሚሆን አመላክተዋል።
ኢትዮጵያ፣ በድርድር የቴክኒክ ኤክስፐርቶች፣ በዋና ተደራዳሪ፣ በንግድ ሚኒስቴሮችና በሀገራት መሪዎች ጉባኤዎች በመሳተፍ ከሌሎች ስምምነቶች በተለየ ሁኔታ ለስምምነቱ ውጤታመነት ከፍተኛ አስተዋፆ ማድረጓን ጠቅሰዋል።
"ኢትዮጵያ በተሳተፈችባቸው ጉባኤዎች ሁሉ ጥቅሟን የሚያስጠብቁና ተጠቃሚነቷን ሊያረጋግጡ የሚችሉ ጉዳዮችን በስምምነቱ እንዲካተቱ ማድረግ ችላለች" ብለዋል።
በእድገት ወደ ኋላ የቀሩ ሀገራት በስምምነቱ በልዩ ሁኔታ እንዲታዩ መደረጉን ጠቁመው ኢትዮጵያ በልዩ ሁኔታ ከሚታዩ ሀገራት ውስጥ እንድትሆን መደረጉን ለአብነት ጠቅሰዋል።
"ታዳጊ ሀገራት በአምስት ዓመት ውስጥ 90 በመቶ የታሪፍ መስመር ዜሮ እንዲያደርጉ በስምምነቱ ተቀምጧል" ያሉት ዳይሬክተሩ ኢትዮጵያን ጨምሮ በልማትና እድገት ወደ ኋላ የቀሩት ሀገራት ደግሞ በ10 ዓመት የታሪፍ መስመራቸውን ዜሮ እንዲያደረጉ በስምምነቱ መቀመጡንም አመልክተዋል።
"በአካባቢያዊ ደረጃ የመጀመሪያ በሆነው ቋሚ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት ለኢትዮጰያ ጥሩ እድሎች ተፈጥረዋል" ያሉት ዳይሬክተሩ በስምምነቱ የተካተቱ 90 በመቶ የሚሆኑ የኢትዮጵያ ምርቶች ከ10 ዓመት በኋላ የታሪፍ መስመራቸው ዜሮ እንደሚሆን ተናግረዋል።
"በስምምነቱ 6ሺህ 372 የሚሆኑ የታሪፍ መስመሮች ያላቸው በ97 ምዕራፍ የተከፈሉ ምርቶች አሉ" ያሉት ዳይሬክተሩ ድርድር የማይካሄድባቸውን በመለየት ለባለድርሻ አካላት ሃሳብ እንዲሰጡበት መላካቸውን አመልክተዋል።
"ስምምነቱ አስተማማኝ የገበያ ዕድል የሚፈጥርና ተጠቃሚ የሚኮንበት ነው " ሲሉም አመላክተዋል።
"ኢትዮጵያ ውህደቱ በሚፈጥረው ምቹ ሁኔታ የተሻለ አገልግሎት እንድታገኝና ተወዳዳሪ እንድትሆን ምክር ቤቱ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነቱን አጽድቋል" ያሉት ደግሞ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ናቸው።
ኢትዮጵያ በስምምነቱ ትግበራ ተገቢውን ጥቅም እንድታገኝና ለስምምነቱ ውጤታማነት ምክር ቤቱ ድጋፍ እንደሚሰጥ አመልከተዋል።
እንደ አፈ ጉባኤው ገለጻ ኢትዮጵያ ከጎሮቤት ሀገራት ጋር እያከናወነች ያለችው የመሰረተ ልማት ትስስር ለነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነቱ ውጤታማነት ወሳኝ ሚና አለው።