ቀጥታ፡

ለአህጉራዊው ጉባዔ ስኬት አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት እውቅናና ምስጋና ተቸረ

አዲስ አበባ ታህሳስ 9/201 (ኢዜአ) ለአፍሪካ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማኅበር /አኖካ/ ጉባዔ ስኬት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት የዕውቅናና የምስጋና መርሃ ግብር ተካሄደ።

የአፍሪካ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማኅበር ሕዳር 27 ቀን 2013 ዓ.ም ጉባዔውን በአዲስ አበባ አካሂዷል።

ጉባዔው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የአህጉሩን ከፍተኛ የስፖርት ሽልማት /ኦርደር ኦፍ ሜሪት/ ማበርከቱም ይታወሳል።

ይህን ጉባዔ ስኬታማ ላደረጉ አካላት እውቅና የተሰጠበትና ምስጋና የቀረበበት ዝግጅት ትናንት ተከናውኗል።

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ ለጉባዔው ስኬት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን አስታውቀዋል።

የመገናኛ ብዙሃን፣ የስፖርት ኮሚሽንና የፌዴሬሽኖች ሚናም ከፍተኛ እንደነበር ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በማኅበሩሽልማቱ የተሰጣቸው ስፖርትን ለማስፋፋት ባደረጉት አስተዋጽኦ እንደነበር ተናግረዋል።

በማሳያነት ለኦሊምፒክ መንደር ግንባታ የተደረገው የሶስት ቢሊዮን ብር ድጋፍና ኢትዮጵያ የአፍሪካ ፓራ ኦሊምፒክ እንደምታስተናግድ ማረጋገጣቸውን አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የእንጦጦን ፓርክ ለመዝናኛና ለስፖርት ማዘውተሪያነት ማመቻቸታቸውንም ዶክተር አሸብር አብነት አቅርበዋል።

የኢትዮጵያን ስፖርት ለማሳደግ የስፖርት አመራሮችና ባለሙያዎች በጋራ እንዲሰሩም ፕሬዚዳንቱ ጠይቀዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ጉባዔው ለኢትዮጵያ ገጽታ ግንባታ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ ጉባዔው በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ መገናኛ ብዙሃን ሚና መጫወታቸውን መስክረዋል።

በዝግጅቱ ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ ለስፖርት በተለይም ለቅርጫት ኳስ መስፋፋት እያበረከቱት ላለው አስተዋጽኦ ዋንጫ ተሸልመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም