ቀጥታ፡

የጣና ሃይቅ ህልውናን ለማስጠበቅ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ የአሰራር መመሪያ መዘርጋት ያስፈልጋል- ባለስልጣኑ

ባህር ዳር ታህሳስ 09/2013 (ኢዜአ) የጣና ሃይቅን ከብክለትና በደለል መሞላት በመታደግ ህልውናን ለማስጠበቅ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ የአሰራር መመሪያ መዘርጋት እንደሚያስፈልግ የአማራ ክልል አካባቢ፣ደንና ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።

"በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር የጣና ሃይቅ ዳር የልማት ስራዎች ተጽዕኖ አማራጭ የልማት ጥናት" በሚል መሪ ሃሳብ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በላይነህ አየለ እንደተናገሩት፤ በጣና ሃየቅ ዳርቻ ያሉ ሆቴሎች፣ ሎጂዎችና ኢንዱስትሪዎች ተረፈ ምርታቸውንና ፍሳሽ ቆሻሻዎችን ወደ ሀይቁ በመልቀቅ ብክለት እያስከተሉ ነው።

ከነዚህ ተቋማት በሃይቁ ላይ የሚለቀቁ ተረፈ ምርቶችም "ፎስፌት"፣ "ናይትሬት" እና "ቢኦዲ" የተባሉ  በካይ ንጥረ-ነገሮች ከሚጠበቀው ደረጃ በላይ ሆነው  መገኘታቸውን ማረጋገጥ መቻሉንም አስረድተዋል።

እነዚህም በካይ ነጥረ ነገሮች በሃይቁ ውስጡ የሚገኘውን ብዝሃ- ህይወት ለአደጋ እያጋለጡ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

ባልተጠና ሁኔታ የሃይቁን ዳርቻ ለተለያዩ ልማቶች እንዲውሉ እየተደረገ ነው የሉት ዶክተር በላይነህ፤ የከተማ አስተዳደሩ በሃይቁ ዳርቻዎች የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች የሃይቁን ህልውና በሚታደግ መልኩ እንዲከናወኑ መመሪያና አሰራር መዘርጋት እንደሚጠበቅበት አስታውቀዋል።

የጣና ሃይቅን ደህንነት ለመጠበቅ በዙሪያው ባሉ የተወሰኑ መሬቶችን ወደ ሃይቁ በመከለል የመከላከያ ደጀን ማልማት እንደሚያስፈልግ በጥናት መረጋገጡንም ገልጸዋል።

የሃይቁን ህልውና ለማስጠበቅ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝም በሃይቁ ዳርቻ የሚጠቀሙ የንግድና የአግልግሎት ሰጪ ተቋማት በህግ አግባብ የአገልግሎት ክፍያ መፈጸም እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

በባለስልጣኑ የአካባቢና ማህበረሰብ ተጽዕኖ  ዳይሬክተር አቶ አበባው አባይነህ በመድረኩ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ እንዳመለከቱት በባህር ዳር ከተማ የሚገኙ ሆቴሎች፣ ሎጂዎችና ሌሎች ድርጅቶች የፍሳሽ ቆሻሻ የሚያስወግዱት ወደ ሃይቁ በመልቀቅ  እንደሆነ በጥናት ተረጋግጧል።  

ድርጅቶቹ ወደ ሃይቁ የሚለቁትን የመጸዳጃ ቤት ፍሳሾችንና ሌሎች ተረፈ ምርቶቻቸውን ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ የማስወገጃ ስርዓት በመተግበር የሃይቁን ዘላቂ ህልውና ለማረጋገጥ የአስራር መመሪያ ማውጣት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በምክትል ርዕሰ መስድተዳደር ማዕረግ የኢኮኖሚ ዘርፍ አስተባባሪ ዶክተር ሰኢድ ኑሩ በበኩላቸው፤ የሃይቁን ዳርቻ መሰረት በማድረግ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙት ተቋማቱ ዘላቂ ተጠቃሚነታቸው የሚረጋገጠው የጣና ሃይቅን ከብክለትና ከደለል መሞላት መታደግ ሲቻል መሆኑን ተናግረዋል።

በጣና ሃይቅ ላይ የሚሰሩ አመራሮች፣ ባለሙያዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን አሰራሩን ለማስፈጸም በቅንጅት በመሥራት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

የባህር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሣህሉ የጣና ሃይቅ የኢትዮጵያ  ትልቁ የውሃ ሃብት እና የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህልውና በመሆኑ ደህንነቱን ለማስጠበቅ የአሰራር  መመሪያ እንደሚያዘጋጁ ገልጸዋልል።

በምክክር መድረኩ  የቀረበው ጥናት ግኝት የሃይቁን ደህንነት አደጋ ላይ እየጣሉ ያሉ መንስኤዎችን በሚገባ አሳይቷል፤ በቀጣይ በጥናቱ የተመላከቱ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ለመተግበር ከተማ አስተዳደሩ ይሰራል ብለዋል።

በባህርዳር ከተማ ትናንት በተካሄደው የምክክር መድረክ የሚመለከታቸው ተቋማት፣ የቢሮ ሃላፊዎች እና የዘርፉ ባለሙዎች ተሳተፈዋልል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም