የህወሓት ጁንታ ያልዋለበትን ገድል ለትውልድ ሲሰብክ ኖሯል.. ሜጀር ጄኔራል ሹማ አብደታ

64

በወንድማገኝ ሲሳይ (ሃዋሳ ኢዜአ)

የህወሓት ጁንታ በስልጣን በነበረበት ዘመን በሀገራችን ህዝብ ላይ ያልፈጸመው ግፍና መከራ የለም ማለት ይቻላል።

በተለይ ኢትዮጵያዊያንን በዘረኝነት ድንበር ለያይቶ የሀገር ፍቅር፣አመለካከትና አስተሳሰብን አኮላሽቷል።

ይህንን በማስመልከት በሀገር መከላከያ ሠራዊት የልዩ ዘመቻዎች ኃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ሹማ አብደታ ጋር ጥቂት ቆይታ አድርጌ ነበር። 

ሜጀር ጄኔራሉ በብላቴ የሚገኘው የልዩ ዘመቻዎች ኃይል ማሠልጠኛ ማዕከል ለ33ኛ ዙር በመሠረታዊ ኮማንዶ ያሰለጠናቸውን የሪፐብሊካን ጋርድ አባላት ሰሞኑን ባስመረቀበት ወቅት በስፍራው በመገኘት የስራ መመሪያም አስተላልፈዋል።

በወቅቱ ያገኘናቸው ሜጀር ጄኔራል ሹማ አብደታ ለኢዜአ እንዳሉት ታዲያ የጁንታው ቡድን የሶስት ሺህ ዘመን ታሪክ ያላትን ታላቋን ኢትዮጵያን በመቶ ዓመት ታሪክ ብቻ በመገደብ ታሪኳን ሲያጠላሽ ቆይቷል።

አዲሱ ትውልድም ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን የአያት ቅድመ አያቶቹን ወርቃማ የኢትዮጵያዊ አልበገር ባይነት ገድሎችን እንዳያውቅ ለማድረግ ተብሰክስኳል።

“በተለይ ‘ተራራውን ያንቀጠቀጠ ትውልድ’ እያለ ያልዋለበትን ሜዳ ትርክት ልብወለድ ለትውልድ ሲሰብክ ኖሯል” ይላሉ።

እንኳንስ ኢትዮጵያዊ፣ ኢትዮጵያዊ ያልሆነ ዜጋ ለማወቅ የሚጓጓውን ተዝቆ የማያልቀውን የሀገራችንን ታሪክ ትውልድ እንዳያውቀው በማድረግ የኢትዮጵያዊነት ስሜትን ለመግደል ያደረገው ከንቱ ጥረት ባይሳካለትም ጁንታው ብዙ ዋትቷል ብለዋል።

ከዚህም ባሻገር የሀገርን ሀብት ዘርፏል፣ በዜጎቻችን ላይ ኢ-ሰብዓዊ ተግባርን ፈፅሟል።ብሄርን ከብሄር፣ሐይማኖትን ከሐይማኖት በማጋጨት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አገራችን እንዳትረጋጋ በማድረግ ብዙ መስራቱን ለአብነት ጠቅሰዋል።

በሠራዊቱ ውሰጥ እርስ በርስ መተማመን እንዳይኖር ማድረግ ብቻ ሳይሆን ጓደኛውን በተኛበት እንዲገድል እስከ ማድረስ የደረሰ አሳፋሪ ተግባር መፈጸሙን ነው ሜጀር ጄኔራሉ የሚናገሩት።

ሰላማዊና ወዳጅ መስሎ እራት ለመጋበዝ ጠርቶ እጅ ላይ ካቴና በማስገባት የሰራዊቱን አባላት በግፍ ማሰቃየቱንና መረሸኑን በቁጭት ያወሳሉ።

የጁንታው ስውር የባርነት ቀንበር ያማረራቸው የሀገራችን ህዝቦች በተባበረ ክንዳቸው ከሥልጣን አሸቀንጥረው ቢጥሉትም በህዝቦች ስም እየማለና እየተገዘተ ህዝባችንን አሰቃይቷል።

ይህ የምድራችን እርጉም ቡድን መቀሌ ውሰጥ በትግራዋይ ጉያ ውሰጥ ተሸሽጎ ሌላ በዘር የተለወሰ የባርነት ቀንበርን በትግራይ ህዝብ ላይ በመጫን በሴይጣናዊ ስውር እጁ የሀገሪቱን ህዝቦች ደም መምጠጡን አላቆመም ሲሉ ይገልጹታል ጁንታውን።

“መንግሥት ሁኔታዎችን ሁሉ እያወቀ የአንድም ዜጋ ህይወት ያለ አግባብ እንዳይጠፋና ለሀገር ሰላም ካለው ቃናኢ አመለካከት በመነሳት ሁሉንም ነገር በሰላም ለመፍታት ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል” ይላሉ።

ሆኖም ገና ከበረሃ ጀምሮ እጁ በህዝብ ልጆች ደም የጨቀየው ይህ አረመኔ ቡድን ከአረሜኔያዊ ድርጊቱ ሊታቀብ አልቻለም።

በተለይ በስውር መንገድ ሀገራችንን በማዳከም እጅና እግሯን አስሮ ለታሪካዊ ጠላቶቿ አሳልፎ ለመስጠትና ሀገራችንን ለመበታተን በቀቢፀ ተስፋ መታተሩን እንደቀጠለበት አዛዡ አመላክተዋል።

ይሔ ጁንታ ጥገኛ ቡድን በሰሜን የነበረውን ሠራዊት በተለያየ መንገድ ሲተናኮል ቆይቶ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ባልታሰበ ሰዓትና ወቅት ታሪክ ይቅር የማይለውን ፍፁም ከሰውኛ አስተሳሰብና ተግባር ውጭ የሆነ ጥቃት መፈፀሙን ገልፀዋል።

ለዚህ ዕኩይ ተግባሩም በተለይ ሠራዊቱን ለመጨፍጨፍ በውሰጣችን የመሸጉትን የጅብ ግልገሎች መጠቀሙን አስታውቀዋል።

በዚህም ጥፋት ያልረካው ይህ ስግብግብ ጁንታ ያልታጠቁትን ንፁሓን ዜጎቻችንን በዘር በመለየት በጭካኔ መጨፍጨፉ የሁድኑን ኢሰብአዊ ድርጊት ትንሹ ማሳያ እንደሆነ ሜጀር ጀነራል ሹማ ይናገራሉ።

“ይህ ድርጊት ታዲያ ሠራዊታችንን ብቻ ሣይሆን ወትሮም መጠቃትን የማይወደውን መላውን የሀገራችንን ህዝቦች አስቆጥቷል” ይላሉ።

በጥቃቱ የተቆጣው አጠቃላይ የሀገራችን ሰራዊት ከውስጡ ፈንቅሎ በመውጣት እሳት እየተፋ በሚንቀለቀል ሀገራዊ ፍቅር ጠላቱን መቆሚያ መቀመጫ በማሳጠት አነደደው።

በባዶ ጉራ የተሞላው የመቀሌው ጁንታ ግፍ በሰራበት ሠራዊታቻን ክንድ ተደቆሰ” ሲሉ በእልህ ይተርካሉ አዛዡ።በዚህ ግዳጅ ውሰጥ ደግሞ የልዩ ዘመቻዎች ኃይልና የሪፐብሊካን ጋርድ አባላት ገድል የላቀና ወደር እንዳልነበረውም በመግለጽ።

እንደሳቸው ገለፃ በክፍሉ ሰራዊት አባላት የተፈፀመው ገድል በእውነታ ዓለም ከሚፈፀመው በእጅጉ የላቀ ነው።

በመሆኑም ስለ ገድሉ ለመተረክ የእውነታ ታሪክ ተራኪነት ሙያን ይጠይቃል ብለዋል።ይህን ድንቅ ኢትዮጵያዊ ታሪክ ልቅም አድርጎ ለመሰነድ እንደ ገድሉ ከፍ ያለ እውቀት እንደሚያስፈል አፅንዖት ሰጥተውታል- ሜጀር ጄኔራል ሹማ አብደታ።

ዘላለማዊ ከብርና ሞገስ ሃገርን ለማዳንና ህግን ለማስከበር በግንባር ቀደምትነት መስዋዕትነትን ለከፈሉ ጀግኖቻችን!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም