የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ዘመናዊ የሃይል መቆጣጠሪያ የልህቀት ማእከል ሊገነባ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ዘመናዊ የሃይል መቆጣጠሪያ የልህቀት ማእከል ሊገነባ ነው
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 08 /2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ዘመናዊ የሃይል መቆጣጠሪያና የልህቀት ማእከል እንደሚገነባ አስታወቀ፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተፈጥሮ ሃብት፣ ውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ቋሚ ኮሚቴ አባላት ኮተቤ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል የእቃ ግምጃ ቤትን ጎብኝተው ጠንካራና ደካማ ጎኖች እንዲሁም መስተካከል ባለባቸው ጉዳዮች ከተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ተወያይተዋል፡፡
ተቋሙ አገልግሎት የማይሰጡ ንብረቶችን በመለየት በጨረታ ሸጦ ከ40 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ማስገኘቱ፣ ለተቋሙ ተሸከርካሪዎች ጥገና የተሟላ ጋራዥ መኖርና ንብረቶቹን ከጉዳት ለማዳን አምስት ዘመናዊ መጋዘኖች መገንባቱን በጥንካሬ ጎኑ ተነስቷል፡፡
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይልና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቀላቅለው የተቀመጡ ንብረቶች ለጥበቃ በማይመች መልኩ መቀመጣቸው አግባብ እንዳልሆነ ተጠቁሟል።
ተቋሙ ያለውን የመሬት ይዞታ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲያውለው የቋሚ ኮሚቴው አስተባባሪ አቶ ዓለሙ ዲንቃ አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አሸብር ባልቻ ዘመናዊ የሃይል መቆጣጠሪያና የልህቀት ማእከል እንደሚገነባ አመልክተዋል።
ማዕከሉን የምስራቅ አፍሪካ ታዳሽ ሃይል የልህቀት ማእከል ለማድረግ ግብ መቀመጡንም ገልጸዋል።
የኮተቤ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል የእቃ ግምጃ ቤት የሚገኘውን ሰፊ ቦታ አገልግሎት ላይ ለማዋል እንደታሰበ ገልጸው፤ “በምስራቅ አፍሪካ ታዳሽ ሃይል ማእከል ማድረግ ስለሆነ አላማችን በቦታው የልህቀት ማእከል ይገነባል” ብለዋል።
የዲዛይን ስራ ማለቁን ገልጸው፤ “በጀት በጅተን ወደ ትግበራ መግባት ብቻ ነው የሚቀረን” ብለዋል።