ኤች አይ ቪ ኤድስን ለመግታት በተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ መስራት ይገባል- ጤና ሚኒስቴር

ሀዋሳ፣ ታህሳስ 08 /2013 (ኢዜአ). የኤች.አይ.ቪ ኤድስ ስርጭትን ለመግታት ለቫይረሱ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ በማተኮር የመከላከል ሥራ ማከናወን እንደሚገባ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ አሳሰቡ ፡፡


"ኤች.አይ.ቪ ኤድስን ለመግታት ዓለም አቀፍ ትብብር ለጋራ ኃላፊነት" በሚል መሪ ሀሳብ ዓለም አቀፍ የፀረ ኤድስ ቀን በሀገራዊ ደረጃ ዛሬ በሀዋሳ ኢንደስትሪ ፓርክ ውስጥ ተከብሯል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ደረጄ በዚህ ወቅት እንዳሉት ኤች.አይ.ቪ ኤድስ በግለሰቦች ላይ ከሚፈጥረው ህመምና ሞት ባሻገር ውስብስብ የሆኑ የማህበረሰብ ችግሮችን የሚያስከትል ነው፡፡

የቫይረሱን ስርጭት በመግታት የሚያስከትለውን ቀውስ ለማስቀረትም ባለድርሻ አካላትን በቅንጅት ከመምራት ባለፈ ህብረተሰቡን በማሳተፍ በተከናወነው የመከላከል ሥራ አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን አስረድተዋል፡፡

ይሁን እንጂ በተገኘው ስኬት በመዘናጋት የመከላከሉ ሥራ እየቀነሰ መምጣቱን ጠቁመው በቫይረሱ የሚያዙ ወገኖች እንዲሁም በኤች.አይ.ቪ ኤድስና ተያያዥ በሽታዎች ምክንያት የሚከሰተው የሞት ምጣኔ እየጨመረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሀገሪቱ ባላት ውስን ሀብት ደረጃውን የጠበቀና ውጤታማ የመከላከል ተግባር እንደሚያስፈልግ ያመለከቱት ሚኒስትር ዴኤታው በተለይ ለቫይረሱ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን መሠረት ያደረገ  ርብርብ ማድረግ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

የፌዴራል ኤች.አይ.ቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ፅጌረዳ ክፍሌ በበኩላቸው ከዚህ በፊት በነበረው የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ተጨባጭ ለውጥ መጥቶ እንደነበር  አስታውሰዋል።

አሁን ባለው መዘናጋት በተለይ አምራች ኃይሉና ለቫይረሱ ይበልጥ ተጋላጭ  የሆኑት የማህበረሰብ ክፍሎች ለጉዳት መጋለጣቸውን አስረድተው ላለፉት አስርት ዓመታት በኢትዮጵያ የቫይረሱ ስርጭት እየቀነሰ መምጣት ሲገባው ባለበት አሀዝ መቀጠሉን ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ብቻ 14 ሺህ 843 አዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መመዝገባቸውን የጠቆሙት ዶክተር ፅጌረዳ ከነዚህም  ከ67 በመቶ በላይ የሚሆኑት ዕድሜያቸው ከ30 ዓመት በታች የሆኑ አምራች የማህበረሰብ ክፍሎች እንደሆኑ ገልጸዋል።

ይህ የስርጭት ሁኔታ በተለይም ለወጣቶች፣ ሴቶችና ሕፃናት ልዩ ትኩረት በመስጠት በተለየ መንገድ ለመከላከል መስራት እንደሚያስፈልግ የሚያመላክት መሆኑን ገልፀው ለዚህም ሁላችንም በቁርጠኝነት ልንረባረብ ይገባል ብለዋል ፡፡

የሲዳማ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ በቀለ ቱንሲሳ በበኩላቸው የኮሮና ቫይረስ ኤች.አይ.ቪ ኤድስን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ላይ ተጽዕኖ ቢያሳድርም  የክልሉ መንግስት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር እየሰራ ነው ብለዋል።

የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል ያሳየነውን የአመራር ቁርጠኝነት በኤች.አይ.ቪ ኤድስም ላይ በመድገም ተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎችን መሰረት ያደረገ ርብርብ ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል።

በሀዋሳ ኢንደስትሪ ፓርክ ውስጥ በተከበረው የፀረ ኤድስ ቀን ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ በኤች አይ ቪ ኤድስ ዙሪያ የሚሰሩ ድርጅቶች ፣የመንግስት አካላትና የፓርኩ  ማህበረሰብ ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም