ቀጥታ፡

ከሱዳን ወደ አገራቸው መመለስ የሚፈልጉ ዜጎችን የመለየት ስራ ሊጀመር ነው - በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 8/2013 ( ኢዜአ) የህወሃት ጁንታ በፈጠረው ችግር ወደ ሱዳን ከተሰደዱ ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው የመመለስ ፍላጎት ያላቸውን የመለየት ስራ ሊጀመር መሆኑን በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ ገለጹ። 

የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል የነበረውን የሕግ ማስከበር አጠናቆ "ወንጀለኞችን የማደንና የመልሶ ግንባታ" ስራ በማከናወን ላይ መሆኑ ይታወቃል።

የህወሃት ጁንታ የፈፀመውን ክህደት ተከትሎ በነበረው የሕግ ማስከበር ሂደት ወደ ጎረቤት አገር ሱዳን የተሰደዱ ዜጎች እንዳሉ ይታወቃል።

አሁን ላይ የህግ ማስከበር ስራው ተጠናቆ የመልሶ ግንባታና ወንጀለኞችን የማደን ተግባር እንዲሁም የሰብአዊ ድጋፎች በመከናወን ላይ ይገኛል።

በመሆኑም በስደት ወደ ሱዳን ከሄዱት ዜጎች መካከል የመመለስ ፍላጎት ያላቸውን የመለየት ተግባር እንደሚጀመር በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ይበልጣል ለኢዜአ ገልጸዋል።

የሚመለሱ ዜጎችን የመለየት ተግባር በሱዳን መንግስትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ የሚከናወን መሆኑንም ተናግረዋል።

በዚህም ስደተኞቹን በማናገር ፈቃደኝነታቸው ተጠይቆ ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት የሕግ ማስከበር እርምጃው በመጠናቀቁና የትግራይ ክልልም ወደ ሰላምና መረጋጋት በመመለሱ የተሰደዱ ዜጎች ወደ አገራቸው ቢመለሱ መንግስት ለመደገፍና መልሶ ለማቋቋም ዝግጁ መሆኑን አምባሳደሩ ገልጸዋል።

ከሱዳን መንግስትና ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ ጋር በተደረገ ውይይትም ሁለቱ አካላት የመመለስ ፍላጎት ያላቸውን ዜጎች በተቻለ ፍጥነት የመለየት ስራን እንደሚሰሩ መግለጻቸውን አመልክተዋል።

ይሁንና ከስደተኞቹ ጋር ተቀላቅለው የገቡ "የሕወሓት ቅጥረኞች" አሁንም ግጭትና ግድያ አለ ወደ አገራችሁ እንዳትመለሱ በማለት የተሳሳተ መረጃ እየሰጡ መሆኑንም ደርሰንበታል ብለዋል።

በመሆኑም ስደተኞቹ ትክክለኛውን መረጃ እንዲያውቁት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ወደ ሱዳን ከገቡ ስደተኞች መካከል የማይካድራውን ጨምሮ በሌሎች የግድያ ወንጀሎች የሚጠረጠሩ ሰዎች ሊገኙ እንደሚችሉም ጥርጣሬ አለን ብለዋል።

መንግስት ዜጎች ወደ አገራቸው ሲመለሱ መልሶ የማቋቋም ተግባር ለማከናወን ዝግጅት እያደረገ ይገኛል ነው ያሉት።

ወደ ሱዳን የተሰደዱት ዜጎች በሀምዳይት፣ ሀሻባና ኡምራኩባ በሚባሉ የስደተኞች ካምፕ ውስጥ እንደሚገኙም ታውቋል።

የሱዳን መንግስትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ ለኢትዮጵያውያኑ የሚያስፈልገውን ድጋፍ እያደረጉ እንደሆነም አመልክተዋል።

ኤምባሲው ዜጎቹ ያሉበትን ሁኔታ በቅርበት እየተከታተለ እንደሆነም አምባሳደሩ አክለዋል።

መንግስት በሱዳን የሚገኙ ስደተኞችን መመለስና መልሶ የማቋቋም ስራን የሚያስተባብር ብሔራዊ ኮሚቴ አዋቅሮ ወደ ስራ መግባቱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም