በሐረሪ ክልል ለ5 የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናትና የባህረ-ጥምቀት ቦታዎች የይዞታ ማረጋገጫ ተሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
በሐረሪ ክልል ለ5 የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናትና የባህረ-ጥምቀት ቦታዎች የይዞታ ማረጋገጫ ተሰጠ
ሐረር፤ ታህሳስ 8/2013 (ኢዜአ ) በሐረሪ ክልል ለሚገኙ አምስት ለሚሆኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት እና የባህረ ጥምቀት ቦታ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ መስጠቱን የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ሃላፊ አቶ አብዱሃኪም አብዱማሊክ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታውን ለቤተ-ክርስቲያኒቱ የምስራቅ ሀረርጌ ሀገረ ስብከት ስራ አስኪያጅ መላዕክ ገነት ቀሲስ ንጋቱ ደሳለኝ ትላንት በተዘጋጀው የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ላይ አስረክበዋል።
የይዞታ ማረጋገጫዎቹን ከክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱሃኪም አብዱማሊክ የተረከቡት የምስራቅ ሀረርጌ ሀገረ ስብከት ስራ አስኪያጅ መላዕክ ገነት ቀሲስ ንጋቱ ደሳለኝ እንደተናገሩት በክልሉ ከ40 እና 50 አመታት በፊት የተሰሩ አብያተ ክርስቲያናት የይዞታ ማረጋገጫ አልነበራቸውም ።
"አብያተ ክርስቲያናቱ የይዞታ ካርታ እንዲያገኙ ቤተ ክርስቲያን ለበርካታ አመታት ጥያቄ ስታቀርብ የነበረ ቢሆንም ምላሽ ሳያገኝ ቆይቷል" ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንዲሰጥ ከተጠየቁት መካከል የአምሰቱ ጥያቄ ምላሽ በማግኘቱ መደሰታቸውን ገልጸዋል።
ጥያቄ ለቀረበባቸው ለቀሪዎቹ አብያተ ክርስቲያናትም የክልሉ መንግስት ምላሽ ለመስጠት ቃል መግባቱን ጠቁመዋል።
ከለውጡ ወዲህ ብዙ ነገሮች እየተሻሻሉ መሆናቸውን ገልጸው "የጥያቄው ምላሽ ማግኘት የክልሉ የለውጥ አስተዳደር ከመጣ ወዲህ የተሻለ መልካም አስተዳደር እንዳለ የሚያመላክት ነው" ሲሉም ተናግረዋል።
የሀረሪ ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱሃኪም አብዱማሊክ በበኩላቸው፤ በክልሉ ለሚገኙ የሃይማኖት ተቋማት እንዲሁም ለትምህርትና ለመንግሥት ተቋማት የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ዘመናዊ በሆነ መልኩ ተዘጋጅቷል።
ከዚህ ውስጥም ለበርካታ አመታት ጥያቄ የነበረው በክልሉ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አብያተ ክርስቲያናት የይዞታ ማረጋገጫ ካርታዎች አንዱ መሆኑንም ጠቁመው በክልሉ ለሚገኙ የመስጂዶችና የአድባራት የይዞታ ማረጋገጫ ካርታም እየተጠናቀቀ ስለመሆኑም አመላክተዋል።