ቀጥታ፡

ለስራ ማስኬጃ የሚወጣለትን ወጪ 25 በመቶ መሸፈን ያልቻለውን የረጲ የደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫን አዋጭ ለማድረግ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 08 /2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በረጲ የደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ የሚደርስበትን ከፍተኛ ኪሳራ ለመቀነስ ከአዲስ አበባ አስተዳደር ጋር እየሰራ መሆኑን ገለፀ።

ኃይል ማመንጫው የሚያስገኘው ገቢ ተቋሙ ለስራ ማስኬጃ የሚያወጣውን 25 በመቶ ያህል እንኳን አይሸፍንም ነው የተባለው።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተፈጥሮ ሃብት፣ ውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በረጲ የደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫና በኮተቤ የንብረት መጋዘን የመስክ ምልከታ አድርገዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አስተባባሪ አቶ አለሙ ዲንቃ ፕሮጀክቱ 50 ሜጋ ዋት ያመነጫል ተበሎ በግማሽ የቀነሰበት ምክንያት እንዲብራራላቸው ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አሸብር ባልቻ የፕሮጀክቱ የማመንጨት አቅም በግማሽ የቀነሰበት ምክንያት በተለያዩ ባለሙያዎችና ኮሚቴዎች ሲጣራ መቆየቱን ተናግረዋል።

በዚህም የተለያዩ ሃሳቦች ከማንፀባረቅ ባሻገር የተሰጠ ወጥ ውሳኔ አለመኖሩን፣ ኮሚቴ ተዋቅሮ ጥናት እየተጠና መሆኑንና የሚቀርበው ውሳኔ ለቦርድ ከቀረበ በኋላ ለሕዝብና ለቋሚ ኮሚቴው እንደሚገለጽ አስረድተዋል።

ረጲ የደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫን የመሰሉ ፕሮጀክቶች በዓለም ላይ በዋናነት የሚገነቡት ቆሻሻ ማቃጠልን ታሳቢ አድርገው መሆኑን ዋና ስራ አስፈፃሚው ገልፀዋል።

ተቋሙ ፕሮጀክቱን በብድር ማስገንባቱንና አሁንም የስራ ማስኬጃ ወጪውን እየሸፈነ አለመሆኑን አንስተው፤ ከፕሮጀክቱ የሚገኘው ገቢ የዚህን ወጪ 25 በመቶ እንኳን መሸፈን እንዳልቻለ አብራርተዋል።

በዚህ ምክንያት ተቋሙ የሚደርስበትን ኪሳራ ለመቀነስ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር ለመስራት ጥያቄ በማቅረብ የጋራ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ረጲ የደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የአዲስ አበባን ደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት ለማዘመንና ከደረቅ ቆሻሻ ኃይል ለማመንጨት ግንባታው በ2006 ዓ.ም ተጀምሮ በ2010 ዓ.ም ነው የተጠናቀቀው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም