ቀጥታ፡

የረጲ የደረቅ ቆሻሻ ሃይል ማመንጫ ጣቢያ ሰራተኞች ጥራቱን የጠበቀ የጤና ደህንነት መጠበቂያ ቁሳቁስ እንዲቀርብላቸው ጠየቁ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 8/2013 ( ኢዜአ) የረጲ የደረቅ ቆሻሻ ሃይል ማመንጫ ጣቢያ ሰራተኞች ጥራቱን የጠበቀ የጤና ደህንነት መጠበቂያ ቁሳቁስ እንዲቀርብላቸው ጠየቁ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተፈጥሮ ሃብት ውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ስር በሚገኘው የረጲ ደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ጣቢያና የኮተቤ የንብረት መጋዘንን  የመስክ ምልከታ አድርገዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት የጣቢያውን ሰራተኞች ባነጋገሩበት ወቅት ሰራተኞቹ  የሰው ኃይል እጥረት አለ፤ የሚገባንን ጥቅማ ጥቅምም በአግባቡ እያገኘን አይደለም ብለዋል።

የሚቀርብልን የጤና መጠበቂያ ቁሳቁስ አቅርቦትም በቂና ጥራቱን የጠበቀ አይደለም ሲሉ ለቋሚ ኮሚቴው ቅሬታቸውን አቅርበዋል።

የሰራተኞች አስተዳደር ሃላፊ አቶ ተስፋዬ አለሙ ለሰራተኞቹ የሚሰጣቸው የጤና መጠበቂያ አበል  ከስራው ከባቢ አንፃር ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

የጣቢያው የጥገና ክፍል ኃላፊ አቶ ገብሬ ኃይሌ በበኩላቸው የመለዋወጫ እቃዎች እጥረት መኖሩን ተናግረዋል።

በቋሚ ኮሚቴው የኢነርጂ ንዑስ ኮሚቴ አባል አቶ ሽመልስ አበባው፤ የሃይል ማመንጫው በዘመናዊነቱ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፤ ለአፍሪካም ተምሳሌት የሆነ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታም የሚያግዝ  ኃይል ከማመንጨት ባሻገር፤ ለዜጎች ሥራ መፍጠሩን ተናግረዋል።

የጣቢያው ሰራተኞች በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 መከሰቱን ተከትሎ የውጭ ዜጎችን በመተካት ጭምር ሥራውን በማስቀጠላቸው አመስግነዋል።

ሰራተኞች ምቹ ባልሆነ የስራ ሁኔታና በአዲስ ቴክኖሎጂ ችግርን ተቋቁመው በመስራት ያሳዩትን ቁርጠኝነትም አድንቀዋል።

ሆኖም ለጣቢያው ሰራተኞች የሚቀርበው ግብዓት በጥራትና በሚፈለገው መጠን መስተካከል ይኖርበታል ብለዋል።

ለሰራተኞች የሚቀርበው የደህንነት መጠበቂያ  አቧራ፣ ሙቀትንና ሽታን የሚቋቋም አለመሆኑና የሰው ኃይል እጥረትም አስቸኳይ እልባት እንዲደረግለት አሳስበዋል።

የሰራተኞችን ጥቅማጥቅምና የተሽከርካሪ እጥረትም መፈታት እንዳለበት አቶ ሽመልስ አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የጄኔሬሽን ኦፕሬሽን ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር እያየሁ ሁንዴሳ፤ የደህንነት መጠበቂያ ለሰራተኛው እንዲቀርብና የሰው ሃይል እጥረቱ አንዲፈታ ለጣቢያው አመራሮች ጥያቄ መቅረቡን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ  በበኩላቸው የተቋሙ  ሰራተኞችን ጥቅማ ጥቅም ለማስጠበቅ እየተሰራ መሆኑንና የጣቢያው ሰራተኞችም ጥያቄ በዚሁ አግባብ ምላሽ ያገኛል ብለዋል።

ከቋሚ ኮሚቴው የተሰጣቸውን አስተያየቶችና ምክረ ሃሳቦች ግብአቶች በመውሰድ የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወሰድም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም