ቀጥታ፡

ወለጋ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ሥራ ጀመረ

ነቀምቴ፣ ታህሣሥ 08 /2013 (ኢዜአ )  በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን የመማር ማስተማር ሥራ ተመራቂ ተማሪዎችን በመቀበል መጀመሩን የወለጋ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።

ተማሪዎች በበኩላቸው ወደ ትምህርታቸው በመመለሳቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር መልካ ሂካ እንዳሉት ተቋርጦ የነበረው የመማር ማስተማር ሥራ የጀመረው ታሕሣሥ 05 ቀን 2013 ዓ.ም ነው፡፡

በ101 የትምህርት ፕሮግራሞች ተመራቂ የሆኑ 3 ሺህ 500 ተማሪዎች  እንዳሏቸው አመልክተው ፤ ለኮሮና  ጥንቃቄ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ባስቀመጠው ፕሮቶኮል መሠረት አንድ የመማሪያ ክፍል እስከ 20 ተማሪዎች ብቻ እያስተናገዱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በየመኝታ ክፍሉም ሁለት ተማሪዎች ብቻ እንዲገቡ፣ የመመገቢያ አዳራሾችና ቤተ መፃሕፍትም ተማሪዎች ርቀታቸውን ጠብቀው መጠቀም በሚችሉበት ሁኔታ መደራጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች አገልግሎት ዳይሬክተር ዶክተር ደረጀ ቶሌራ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ከሩቅ ለሚመጡ ተማሪዎች የትራንስፖርት አገልግሎትን ከማመቻቸት ጀምሮ በሌሎች የአገልግሎት መስጫ ቦታዎች የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በሚያስችል መልኩ መዘጋጀታቸውን አስረድተዋል፡፡

ወደ ትምህርታቸው ከተመለሱት ተመራቂ ተማሪዎች መካከል የሶስተኛ  ዓመት የኢኮኖሚክስ ትምህርት ከፍል ተማሪ ካሣሁን ካፒቴን በሰጠው አስተያየት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የመማር ማስተማሩ ሥራ በመጀመሩ መደሰቱን ገልጿል፡፡

የኮሮና ቫይረስን እየተከላከሉ ትምህርታቸውን ለመማር እንዲችሉ የእጅ መታጠቢያ ቦታዎች መዘጋጀቱንና ጭምብልም እንደተሰጣቸው ተናግሮ እሱን በአግባቡ እየተጠቀሙ መሆናቸውን ገልጿል፡፡

የኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ የአምስተኛ ዓመት ተመራቂ ተማሪ አብዲ ጋሩማ በበኩሉ ከዘጠኝ ወራት በኋላ ወደ ትምህርቱ በመመለሱ ደስተኛ መሆኑን ገልጾ  ዩኒቨርሲቲው በጥሩ ዝግጅት እንደተቀበላቸው  ተናግሯል፡፡

የሶስተኛ ዓመት የሎጂስቲክስ ተማሪ ሜቲ ፈቀደ በበኩሏ የተማሪዎች የአገልግሎት መስጫ ቦታዎች ሁሉ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በሚያስችል ሁኔታ መዘጋጀቱን ተናግራለች፡፡

ከቫይረሱ ተጠንቅቀን በመማር ትምህርታችንን ጨርሰን መመረቅ እንፈልጋለንም ብላለች።

ተማሪዎች በየቦታው በተዘጋጀላቸው የእጅ መታጠቢያ ቦታዎች እጃቸውን እንደሚታጠቡ፣ የተሰጣቸውን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል  በመጠቀም ኮሮናን ለመከላከል ጥንቃቄ እያደረጉ ትምህርት መጀመራቸውን አሰተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም