ቀጥታ፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከተባበሩት መንግስታት የስነ ህዝብ ፈንድ የኢትዮጵያ ተወካይ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 8/2013(ኢዜአ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከተባበሩት መንግስታት የስነ ህዝብ ፈንድ የኢትዮጵያ ተወካይ ዴኒያ ጋይሌን ጋር ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተወያዩ፡፡

በውይይቱም አቶ ደመቀ ባደረጉት ገለጻ መንግስት በትግራይ ክልል የወሰደውን የህግ ማስከበር ዘመቻ ንጹሃን ሳይጎዱ ማከናወኑን ጠቅሰው፤ የሥነ ህዝብ ፈንዱ በሱዳን ላሉት ሴት ኢትዮጵያውን ስደተኞች ላደረገው ድጋፍም አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት መንግስት በትግራይ ክልል እያካሄደ የነበረውን የህግ ማስከበር ዘመቻውን አጠናቆ ሰብዓዊ ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ለዴኒያ ጋይሌ አስረድተዋል።

ከሰብዓዊ ድጋፍ ጎን ለጎንም የወደሙ መሰረተ ልማትን መልሶ የመገንባትና ወንጀለኞችን አድኖ ለህግ የማቅረብ ምዕራፍ ላይ መደረሱንም አቶ ደመቀ አብራርተዋል።

ዴኒያ ጋይሌ በበኩላቸው የተባበሩት መንግስታት የስነ ህዝብ ፈንድ በትግራይ ክልል ላሉ ህጻናትና ሴቶች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ለመቀጠል ማቀዱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም