የሃይማኖት ተቋማት ለሠላም እና አንድነት ግንባታ አስተዋጾአቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው ተመለከተ - ኢዜአ አማርኛ
የሃይማኖት ተቋማት ለሠላም እና አንድነት ግንባታ አስተዋጾአቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው ተመለከተ
ሐረር፣ ታህሳስ 08 /2013(ኢዜአ) በሀገሪቱ ሠላምና ህብረብሔራዊ አንድነት ግንባታ ላይ የሃይማኖት ተቋማት እያበረኩቱት ያለው አስተዋጽኦ ማጠናከር እንዳለባቸው ተመለከተ።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሰላም፣ አብሮነት፣ ሃይማኖታዊ ጉዳይ እና ብዝሃነት ዙሪያ በሐረር ከተማ የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው።
በመድረኩ የተገኙት የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ እንደተናገሩት፤ የምክክር መድረኩ በሀረር ከተማ መካሄዱ የክልሉ ነዋሪዎች ተከባብረው በአብሮነት በመኖር የሚታወቁባቸውን መልካም እሴቶች ወደ ሌሎች አካባቢዎችም ለማስፋት ያግዛል።
በክልሉ በተለይም ከለውጡ ወዲህ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በማረም ህዝቦችን ወደ ቀደመ ታላቅነት የሚያሸጋግሩ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።
የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሀገሪቱ ፅንፈኝነትን በመከላከል ሰላምና አብሮነት እንዲጎለብት እንዲሁም ጠንካራ ህብረብሄራዊ አንድነት እንዲጎለብት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ተቋሙ እያከናወነ ያለውን ይሄን በጎ ተግባር አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበትም አመልክተዋል።
የሃይማኖት ተቋማት ዜጎችን እያስተማሩ በመልካም ሥነ-ምግባር በማነፅ በሰላም እና መከባበር እንዲኖሩ ከማድረግ አንፃር ጉልህ ሚና አላቸው ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሀፊ ሊቀ ትጉሃን ታጋይ ታደለ ናቸው።
ከዚህ አንፃርም የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከተመሰረተ 2003 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል ብለዋል።
ጉባኤው በየክልሉ የተነሱ አለመግባባቶችን በየክልሉ ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በርካታ ግጭቶች በእርቅ እንዲፈቱ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል።
የእርስ በእርስ ግንኙነቶች ጥያቄ ውስጥ የገባባቸው አካባቢዎችን በጥናት በመለየት ችግሮች እንዲፈቱና በማህበረሰቦቹ መካከል መተማመንን እንዲሰፍን ማድረግ መቻሉን ሊቀ ትጉሃን ታጋይ ተናግረዋል።
ግጭቶች ከመፈጠራቸው አስቀድሞ መከላከል ላይ አተኩሮ መስራት አስፈላጊ መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ጸሀፊው፤ የሃይማኖት አባቶች፣ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎችና ባለድርሻ አካላት የዜጎችን የመተባበርና የአንድነት እሴት ማስቀጠል ላይ አትኩረው መሥራት ይገባቸዋል ብለዋል።
የሀረሪ ክልል የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰብሳቢ መጋቢ መስፍን በየነ በበኩላቸው፤ለዘመናት በዘለቁ ጊዜያት ለተጋመዱና ለተሳሰሩ እሴቶቻችን ዋጋ መስጠት አስፈላጊ ነው ብለዋል።
በአውደ ምህረቶችና በመስጂዶች ከምንጊዜውም በላይ ሰላምና አብሮነትን በመስበክና በማስተማር ህዝቡ በተለይም ወጣቱ የሰላም አምባሳደር እንዲሆን ማስቻል እንደሚገባ አመልክተዋል።
የክልሉን የሰላም፣ የፍቅርና የአብሮነት እሴት እንዲጎለብት የክልሉ ነዋሪዎች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
በሐረር ከተማ ከትናንት ጀምሮ እየተካሄደ ባለው የምክክር መድረክ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሀይማኖት አባቶች ፣አባገዳዎችና ወጣቶች እየተሳተፉ ነው።