ኢትዮጵያዊነት - የማይለዋወጥና የማይደበዝዝ ማንነት

47

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 8/2013 ( ኢዜአ) ኢትዮጵያዊነት - የማይለዋወጥና የማይደበዝዝ ማንነት

ኢትዮጵያዊነት - የማይለዋወጥና የማይደበዝዝ ማንነት

                                               ከብርሃኑ ተሰማ /ኢዜአ/

"እንጀራ ልጋግርለት"

በቅርቡ ነው የደቡብ ክልል ቴሌቪዥን በወቅታዊው የአገር ጉዳይ ለመከላከያ ሠራዊት እየተደረገ ስላለው ድጋፍ፤ ስለ ሠራዊቱም የሕዝብ አስተያየት የዘገበውን ያስተላልፋል። ከበርካታ አስተያየቶች የአንዲት እናት ንግግር ውስጤን ነካው፤ በእጅጉ የመሰጠኝ የእኚህ እናት አስተያየት ለሠራዊቱ ያላቸውን ፍቅርና ክብር ለመግለጽ ላደርገው እችላለሁ ያሉት ነው "ለመከላከያችን እንጀራ በጋገርኩለት" አሉ።

አዎን ሰው ካለው ቀንሶ ይሰጣል። እኚህ እናት ደግሞ ያላቸው ጉልበት ይሆናል። ለዚህ ነው ባላቸው፣ በሚችሉት አቅም ተሳትፎ በማድረግ የአገር መከላከያ ሠራዊቱን ለመደገፍ ቆርጠው የተነሱት። የሠራዊቱን አባላት ትኩስ እንጀራ እየጋገሩ ሊያበሉት። እኚህ እናት ገንዘብም፣ ደምም፣ የእርድ እንስሳም ሆነ ሌሎች ነገሮችን ከለገሱት ኢትዮጵያዊያን የሚበልጥ እንጂ ያላነሰ ድጋፍ ለማድረግ ነው ለአገራቸው ቃል የገቡት። ወልደው እንዳሳደጓቸው ልጆቻቸው ሠራዊቱን ባለበት ሄደው ትኩስ እንጀራ ጋግረው ማብላት ይፈልጋሉ።

የእሳቸው ምኞት ከሠራዊቱ ጎን በተግባር ተሰልፈው የአገር ጠላቶችን ለመደምሰስ የተካሄደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ በድል እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ማድረግ ነው።

ክህደት የተፈፀመበት የአገር መከላከያ ሠራዊት አገር ለማፈራረስ የተነሱትን የታሪክ ጉድፎች ለማጽዳትና ወንጀለኞችን ወደ ሕግ ለማቅረብ ግዳጅ ላይ በመሆኑ እንጀራ የሚያገኝበት ሁኔታ የለም። ስምሪቱ በደረቅ ስንቅ የተገደበ ነው። እንጀራ ከተገኘ መልካም ነው ነገር ግን ቦታውም፤ ያለበት ነባራዊ ሁኔታም ለዚህ ምቹ ስለማይሆን 'ለጊዜው ይለፈኝ' ማለቱ የግድ ነው። ከዐውደ ውጊያው መንደር እየተሰማ ያለው አለኝታህ ነኝ በማለት ከሕዝቡ የተበረከቱለትን ሰንጋዎቹን የሚያርደው ከድል በኋላ እንደሆነ ነው።

በዱር፣ በገደሉ፣ በጫካና በየሸንተረሩ የሚፋለመው ሠራዊት ሕግ የማስከበር ስራውን እያከናወነ ያለው ኮቾሮ ብስኩቱን በውሃ ከተገኘም በሻይ እርጥቦ በመመገብ ነው። ስንቁ ይሄ ነው። ቀለቡ የአገርና የሕዝብ ፍቅር ነው ማለት ይቻላል። አገሩንና ሕይወቱን የሚገብርበት ትልቁ ዓላማ የአገሩ ነፃነት፣ ልማትና የሕዝቡ ሠላም ነው።

አሁን አምባገነኖችን ለማንበርከክ እያደረገ ባለው ተጋድሎ እንጀራ ቢናፍቀውም ያንን ለማግኘት ሁኔታዎች ምቹ አይደሉም። ደግሞም ትግሉ ከሚዋጋው ኃይል ጋር ብቻ አይደለም። ከአየር ፀባዩና ከመልክዓ ምድሩም ጭምር እንጂ። ለዚህ ነው አመጋገቡን ከውሃና ብስኩት ጋር የተያያዘ የሚያደርገው።

ወታደር ሲቀጠር ጀምሮ ትኩስ እንጀራ የሚያገኝበት ሁኔታ ብዙም አይደለም። አንደ አገሩና እንደ ባህሉ የለመደውና ያደገበት እንጀራ ቢሆንም በተለይ በአሁኑ ወቅት ሕግ የማስከበር ዘመቻውን ተከትሎ ለተወሰኑ ጊዜያት ከእንጀራ መራራቁ የግድ ነው። ግዳጅ ላይ ነውና ለጊዜው አይናፍቀውም። የእማማን ትኩስ እንጀራ የሚበላበት ቀን ግን ሩቅ አይሆንም።

ትናንት አገሩን ለመጠበቅ ከውጭ ጠላቶችና አሸባሪዎች ጋር የተዋጋው፤ ዛሬ ደግሞ የውስጥ ጉድፎችን ለማጥራት በዱር በገደሉ እየተዋደቀ ያለው የመከላከያ ሠራዊት አንዲት ሕይወቱን ለአገሩና ለሕዝቡ መስዋዕት እያደረገ ያለው ረሃብና ጥሙን ተቋቁሞ ነው። 

እሱ ለሌሎች ሻማ ሆኖ እየቀለጠ ነው ማለት ይቻላል። እንጀራ አገር ሲረጋጋና ግዳጁ ጋብ ሲል የሚያገኘው የ'ቅንጦት' ምግቡ ነው። እስከዚያው ግን ከኢትዮጵያዊያን ደረቅ ስንቅ ከየአቅጣጫው ይጎርፍለት ጀምሯል። በሶ በሉት ጭኮ፣ ድርቆሽ በለው ዳቦቆሎ ለሠራዊቱ እየደረሱለት ነው። በዚህ ሠዓት የኢትዮጵያ ሕዝብ የመከላከያ ሠራዊቱን ለመቀለብ ኮንትራት ፈርሟል ማለት ይቻላል። በዚህች ዓለም መንግሥት ቀጥሮ በጀት የመደበለትን ሠራዊት በራሱ አስተዋጽኦ የሚመግብ ሕዝብ ያለበት ሌላ አገር ያለ አይመስለኝም። 

ለውጡና ነውጡን የተሻገረው

አገሪቷ ላለፉት ሦስት ዓመታት ያህል በለውጥ ሂደት ውስጥ ነች። ለውጡ ያመጣውን ነፃነት አንዳንዶች ወደ ሥርዓት አልበኝነት ቀይረውት ሠላምና መረጋጋት ሲያሳጡን ቆይተዋል። መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር በወሰዳቸው እርምጃዎች ሕግና ሥርዓትን ብቻ ሳይሆን የአገር ህልውናን ማቆየት እንደተቻለም ይታወቃል።

ከካቻምና አምና፤ ከአምና ዘንድሮ እየገጠሙን ያሉ ፈተናዎች የውጭና የውስጥ ኃይሎች በጋራና በተናጠል በሚያደርጉት የተቀናጀ እንቅስቃሴ መሆኑን የማያውቅ ኢትዮጵያዊ አለ ማለት ይቸግረኛል።

ለውጥ ሾተላይ በሚሆንባት አገር ትዕግሥትን ከመቻቻል ጋር በሠላማዊ መንገድ ለማካሄድ ዕድል የሰጠውን አመራር ለመቀበል ያቃታቸው የሥልጣን ጥመኞች፣ ከፋፋዮችና አገር አፍራሾች እንቅልፍ አጥተው ሲሰሩ እንደነበር ከእኛ ውጭ ምስክር የለም።

እነዚህ ኃይሎች በተወሰኑት የአገሪቱ ክፍሎች የለውጡን ኃይል በመቀናቀን ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ሲያደርሱ ቆይተዋል። በዚህም የሞተና የቆሰለው፣ የአካል ጉዳት የደረሰበትና የወደመው ንብረት ቀላል አልነበረም።

ህወሓትና መሰሎቹ ለ27 ዓመታት በበላይነት ባስተዳደሯት አገር ኢትዮጵያዊነቱን ሳያውቅ በብሔርተኝነት ተቀርጾ አገሩን የማያውቅ ትውልድ በአንድ በኩል፤ የዘመኑ ንፋስ ያልወሰዳቸው ኢትዮጵያዊያን በሌላ በኩል ቆመው የጥንታዊና ታሪካዊዋን ኢትዮጵያን ህልውና ለማስቀጠል ትግል የገጠሙትም በለውጡ ዘመናት ነበር። የአገር ህልውና ፈተና ላይ ወድቆ 'ይቺ አገር ወዴት እየሄደች ነው?' ሲያሰኙን ቆይተዋል።

በዚህ ላይ በየጊዜው እዚህም እዚያም በሚለኮሱ ብሔርና ማንነት ላይ ያተኮሩ ጥቃቶች የጋራ አገር የሌለን እስኪመስለን ድረስ ቆሽታችንን አድብነውት ለዜጎቿ የማትመች አገር ባለቤት መሆን ሳይሆን ኢትዮጵያ የምትባል አገር ዜጎች መሆናችንን እንድንጠራጠር አድርጎን ነበር። የሚያራኩተንና የጥፋት ምንጩ የት እንዳለ ብናውቅም የያዘ ይዞን ቆይቷል። 

"ጁንታው" እና መሰሎቹ ያልበገሩት ማንነት

"ስግብግቡ ጁንታ" የህወሓት የጥፋት ቡድን የማይነካውን በመንካት የመቃብር ጉዞውን የሚያስቀጥልበትን መንገዱን ጠረገ። ላይመለስም ወደ ግብዓተ መሬቱ ጫፍ ማዝገሙን እንደቀጠለ ነው።

ከራስ አልፎ ለአፍሪካዊያን ወንድሞቹና እህቶቹ ሠላም መረጋገጥ የሰራው፣ ለሕዝቦች ነጻነትና እኩልነት የቆመው ሠራዊት በገዛ ወገኖቹ ግፍ ተፈፀመበት። የህወሓት የግፍ ጽዋ እየሞላ ነበርና የመከላከያ ሠራዊቱ ልዩ ኃይሎችና ሚሊሺያዎችን ከጎኑ አሰልፎ የገቡበት ገብቶ ሊያዳሽቃቸው ክንዱን አስተባብሮ ተነሳ፤ እናም አደረገው።

የአገሬ ሕዝብ ከ1990 እስክ 1992 በተካሄደው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት የተሳተፈው ዛሬ በከፋፋይነትና የራሱን ጥቅም ማጋበስ እንጂ ኢትዮጵያዊነትን በአግባቡ ባልተረዳው ባንዳ ኢትዮጵያዊነት ፈተና ውስጥ በገባበት ጊዜ ቢሆንም፤ ሕዝቡ ያኔም በዜግነቱ የሚኮራ መሆኑን በተግባር አሳይቷል።

ሶማሊያ በኢትዮጵያ ላይ ከ1969 እስከ 1970 ዓ.ም በከፈተችው ጦርነት በወቅቱ አገሪቷን ይመራ የነበረው ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ወይም ደርግን የሚቃወሙ የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ አደባባይ ብቅ ያሉበት የአብዮት ወቅት ነበር፡፡ አብዮትና ፀረ-አብዮት በሚል የተከፈሉት ጎራዎች ወራሪውን ኃይል ለመመከት ወደኋላ አላሉም፡፡ በአንድነት ተነስቶ ዳር ድንበሩን ያስከበረ ሕዝብ ያኔም ነበረ፤ ያኔም ኢትዮጵያዊነት ጎልቶ ታይቷል። 

የጣልያን ወረራን መክተው ለቅኝ ገዥዎች አልገዛ ብለው ለአምስት ዓመታት በዱርና በገደል፣ ሐሩርና ውርጭ ተቋቁመው ፋሺስት ጣልያንን አሸንፈው በነፃነቷ የኮራች አገር ለትውልድ ያስረከቡት ኢትዮጵያዊያን አንድነታቸውን አጥብቀው የጋራ ጠላታቸውን ተዋግተው ነበር፡፡ በፊውዳሉ ሥርዓት የተከፉና የተገፉ ኢትዮጵያዊያን በ1920ዎቹ ነበሩን፡፡ "ከአገር በላይ ምን አለ" በማለት የሆዳቸውን በሆዳቸው ይዘው ለድል በቅተዋል፡፡

አውሮጳዊያን አፍሪካን እንደ ቅርጫ ለመከፋፈል ሲነሱና ጣልያንም ኢትዮጵያን በገጠመችበት ከ125 ዓመታት በፊት በተካሄደው የአድዋ ጦርነት የአሸናፊነት ምስጢር አንድነት ነው።

ከየአቅጣጫው ተጠራርቶ ወደ ትግራይ የተጓዘው የዘማቹ ኃይል መሪዎች እርስ በርስ መናቆራቸውን ያቆሙት ወራሪው የያዘው የአገራቸውን መሬት፣ የደፈረው ክብር የሕዝባቸው መሆኑን አውቀው "እምቢ ለነፃነቴ!" ብለው በህብረት በመቆማቸው ነበር። ዛሬስ ብንል? በክልል አስተሳሰብ ታጥረው ኢትዮጵያዊነት የማይመቻቸው፣ ኢትዮጵያዊነትን ለጥቅም ካልሆነ በቀር የማይፈልጉ፣ የሌሎች ህልውና የሚመሰረተው በእነርሱ ፈቃድ ብቻ አድርገው ክልላዊነትን ያነገሱ፣ ከእነሱ አስተሳሰብና አመለካከት ውጭ የሆነውን ለመቀበል የማይሹና የማይችሉ፣ በተለወጠችና አንድ እየሆነች በመጣች ዓለም መለወጥ ያልቻሉ ጉዶች ገጥመውናል።

ለሰው ልጆች ክብር የሌላቸው ሰው በላዎች የትጥቅ ትግል ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ የሐሳብ ልዩነት ያላቸውን ሁሉ ደብዛቸውን ሲያጠፉ ኖረዋል። የሀሳብ ልዩነት ማለት ጠላትነት እንዳልሆነ በሕገ መንግሥት ጭምር ቢነግሩንም አፈጻጸሙ ግን የተገላቢጦሽ እንደነበረ ለዓመታት በተግባራቸው አሳይተውናል።

ታዲያ የሰው መልክ ይዘው ተግባራቸው የሰይጣን የሆነው የህወሓት የጥፋት ቡድን አባላት አብሯቸው በኖረና ኢትዮጵያን ብሎ የአገሩን ዳር ድንበር ባስከበረ የመከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት በመፈጸም በዓለም የከሃዲዎች መዝገብ ሂትለርና ሙሶሎኒን የተቀላቀሉበትን ታሪክ አስመዝግበዋል፡፡

ይህን አሳፋሪ ጀብዳቸውን ደግሞ "መብረቃዊ ጥቃት ፈጸምን" በማለት በአደባባይ ለፍፈዋል። ፍርዳቸው በዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት ሊሆን እንደሚችል በራሳቸው ፍንጭ ሰጥተዋል።

ለእነሱ "ኢትዮጵያዊነት" ከእነሱ ጋር መሆንና የጥፋት ዓላማቸውን ማራመድ ነው። መከላከያ ሠራዊት ባካሄደው ዘመቻ አቅማቸው ተዳከመ እንጂ ሌላ ጭፍጨፋ በመፈፀምና አገር በማቃጠል ፍሙን እየሞቁ መኖር ይመርጣሉ። አይሆንም እንጂ!!!

እናም ይህን በአግባቡ የተረዳው የአገሬ ጀግና ሕዝብ የከሃዲውን የህወሓት ቡድን ተግባርና ፍላጎቱን በሚገባ ስላወቀ ክንዱን አስተባብሮ የገባበት ጉድጓድ ገብቶ ዋጋዋን እየሰጠው ነው። ድባቅ በመምታት መቃብሩንም እያፋጠነው ነው።

ካለፈው ጥቅምት ማብቂያ ወዲህ በኢትዮጵያ ያልተጥለቀለቀ የለም። ከተሞች መጀመሪያ በመከላከያ ሠራዊት ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ለማውገዝ ኋላም ሠራዊቱ በመልሶ ማጥቃት እያስመዘገበ ያለውን ድል ለማሞገስ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርገው በሚያውለበልቡ ሰልፈኞች ተጥለቀለቁ። 

የእርድ እንስሳት በተለይ ሰንጋ በሬዎች ከአራቱም የአገሪቷ ማዕዘናት በአዲስ አበባ የምድር ኃይል ቅጥር ግቢን ማጥለቅለቃቸውን ሁለት በሉ። ይህኛው ከክልሎች ተሰባስቦ ወደ ማዕከል የተላከው ነው። ለሕግ ማስከበር ዘመቻው ቀረብ ካሉት አካባቢዎች በቀጥታ የተላከውን አያካትትም። በአርሶ አደሩ እጅ ደልበው ያለ ስስት የተለገሱትን በሬዎች "የሰንጋዎች ሱናሚ" ማለት ይቻላል።

ሌላው የገንዘብ ድጋፍ ነው፤  ከአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ፣ከክልሎች፣ ተቋማት፣ ማህበራትና ግለሰቦች የተሰባሰበው ድጋፍ ከፍተኛ ነው።

የደም ልገሳው ወደር የሌለው ሆኖ ቀጥሏል። እንደ ዓይኑ ብሌን የሚሳሳለትን የመከላከያ ሠራዊቱን ለመደገፍ ብዙዎች "ኢምንት" ያሉትን ደም ተራ ጠብቀው በመለገስ ላይ ናቸው።

በቀጣይ ብቅ ያለው ደግሞ የደረቅ ስንቅ ስጦታ ነው። ሴቶቻችን በሶ፣ ድርቆሽ፣ ጭኮ፣ ዳቦ ቆሎ፣ ቆሎና በርበሬ አዘጋጅተው ለሠራዊቱ መላክ ጀምረዋል። ይህ ቀጣይ እንደሚሆን ይጠበቃል። ከፍ ያለው መጠን ቅቤ፣ በጎችና ፍየሎች እንዲሁም ዶሮዎች በስጦታ እየጎረፉ መሆናቸውንም አስታውሱልኝ። 

ሠራዊቱ ጁንታውን ለፍርድ ለማቅረብ የጀመረውን የሕግ ማስከበርና የህልውና ዘመቻ ምዕራፉን በድል ተወጥቶታል። እነ እንቶኔ አገር እየመዘበሩ ጮማ መቁረጥና ውስኪ መጠጣት ሊቀርብን ነው ብለው ሕዝብን መጠቀሚያ ማድረጋቸውም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይቀራል። ሕይወቱን ለአገርና ለሕዝብ ክብር የሰጠው ቆፍጣናው የአገር መከታ መከላከያ ሠራዊት "ሰንጋውን ከድል በኋላ" ብሎ ለራሱ ቃል ገብቷል። ወንጀለኞችን የማደንና የመልሶ ግንባታ ምዕራፍ ቀጥሏል፤ በዚህም ሌላ ድል አለ።

ሲጠቃለል

ኢትዮጵያዊያን ዛሬም አንድነታቸውን በማያዳግም መልኩ ያሳዩበትን አጋጣሚ ጁንታው ባልተጠበቀ ሁኔታ ፈጥሯል። "ጠላት ከሩቅ አይመጣም" እንዲሉ የህወሓት ቡድን ድብቅ ማንነትና ሴራ በአደባባይ በግላጭ ወጥቷል። ኢትዮጵያዊያን በመስዋዕትነት፣ በአንድነት ሆነን የማንለያይ መሆናችንን ለዓለም አሳይተናል። "ኢትዮጵያን የነኳት ይፈርሱ እንደሆን እንጂ አትፈርስም" የተባለው አለነገር አይደለምና እየተፈፀመ ነው።

ጥንትም፣ ዛሬም፣ ነገም አንድነት ኃይል ነው!!! ኢትዮጵያዊነት ደግሞ ትክክለኛ መገለጫው!!! 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም