ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገለት

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 7/2013(ኢዜአ) ሂዩማኒቲ ኤንድ ኢንክሉዥን የተባለው ዓለም አቀፍ ተቋም ለኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የተለያዩ መገልገያ ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገ።፡ 

ድጋፉን ያደረገው ሂዩማኒቲ ኤንድ ኢንክሉዥን በጤና፣ በትምህርት እና በማህበራዊ አገልግሎት ዘርፍ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ  በአፍሪካና በሌሎች አህጉራት ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን የህብረተሠብ ክፍሎች ለመደገፍ የተቋቋመ ዓለምአቀፍ  ተቋም ነው።

ተቋሙ በኢትዮጵያ ሄላሲያ የተሰኘውን ፕሮጀክት በመቅረጽ ቀጣይነት ያለው ድጋፎችን ያደርጋል።

በአፍሪካ የጤና፣ ትምህርት እና አካታች ፕሮጀክት ተወካይ አንተነህ ዳርሰማ በኖርዌይ መንግሥት በተገኘ ድጋፍ የቁሳቁስ እገዛው መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

በእለቱም ለአካል ጉዳተኞች አጋዥ የሆነ ተሽከርካሪ፣ ለቢሮ አገልግሎት የሚውሉ የተለያዩ ቁሳቁሶች ድጋፍ ተደርጓል፡፡

በቀጣይም ድጋፉን በማጠናከር ባለሙያ የማሟላት እንዲሁም ቴክኒክ ሥልጠናዎችን ተደራሽ እንዲሆኑ ይደረጋል ብለዋል፡፡

የሳኒታይዘር፣ ማስክ፣ ፈሳሽ ሳሙና እና ሌሎች የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፎችንም አበርክቷል።

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አባይነህ ጉጆ ድጋፉ በማህበራቱ ፍላጎት ላይ ተመስርቶ በመሆኑ የጎላ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሂዩማኒቲ ኢንክሉዥን ፕሮግራም ዳይሬክተር ሚስተር ጀሮን ስቶል በበኩላቸው፣ ተቋሙ ለ30 ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልፀው፤ ዛሬም የተደረገው ድጋፍ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

በቀጣይም ሁላችንም  ያለንን ልምድ ተጠቅመን ልንሰራ ይገባል ነው ያሉት፡፡

የተለያዩ የአካል ጉዳተኛ ማህበራት ተወካዮችም በተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በሀገሪቱ ሦስት ክልሎች የሚገኙ አካል ጉዳተኞች ማህበራትን ለቀጣይ ሁለት ዓመታት ድጋፍ የማድረግ ሥራ እንደሚከናወን ጠቁመዋል፡፡

ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በአራት አፍሪካ ሃገራት ተመሳሳይ ድጋፍ እንደሚያደርግም  ከቢሮው  የተገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም