ቀጥታ፡

የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ በአዲስ አበባ ከሚኖሩ የትግራይ ክልል ተወላጅ ወጣቶች ጋር ውይይት አደረገ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 07/2013 (ኢዜአ) የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ በአዲስ አበባ ከሚኖሩ የትግራይ ክልል ተወላጅ ወጣቶች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አደረገ።

ውይይቱ በክልሉ በተካሄደው የህግ ማስከበርና መልሶ በመገንባት ሂደት ላይ የወጣቱ ሚና እና ተሳታፊነት ምን መሆን እንዳለበት ለማሳየት ያለመ ነው።

የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካና ሲቪክ ጉዳዮች ዘርፍ ሃላፊ ዶክተር አለሙ ስሜ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ የህወሃት ጁንታ የለኮሰው እሳት ንጹሀንን ሳያቃጥል በጥንቃቄ እና በጥበብ በተመራ ዘመቻ በድል ተጠናቋል።

"እብሪት አገር ያጠፋል እብሪት እራስንም እንደሚያጠፋ ከጁንታው ልንማር ይገባል" ብለዋል።

ህግ በማስከበር ዘመቻው የተገኘው ድል የሁሉም ኢትዮጵያውያን መሆኑን ጠቁመዋል።

“የኢትዮጵያ ህዝብ ነው ያሸነፈው ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ ጁንታውን ባለመደገፍና ባለመሰለፍ አስተዋጽኦ አድርጓል” ብለዋል።

ከድል በኋላ እብሪተኛ መሆን እንደማያስፈልግ ገልጸው፤ “የህወሃት ጁንታ ሁሉንም ዜጎች እና ህዝቦች የበደለ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

በስልጣን ላይ ያሉ የአንድ መንደር ልጆች መጠቀማቸውንም ተናግረዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ምክትል ሊቀመንበር አክሊሉ ታደሰ የህወሃት ጁንታ የብልጽግና ፓርቲ እንዳይመሰረት በርካታ ጥረቶችን ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሷል።

ህወሃት የዘረጋውን የመከፋፈልና የመለያየት መንገድ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን በማጠናከር ወጣቶች አጥብቀው መታገል እንዳለባቸው አስገንዝቧል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የህወሃት ጁንታ በሰሜን እዝ የሰራዊት አባላት ላይ ያደረሰውን ጥቃት አውግዘዋል፡፡

የህወሃት ጁንታ ሃላፊነት የማይሰማው አገር አፍራሽ መሆኑን ተከትሎ ታሪክ ይቅር የማይለው ተግባር መፈጸሙን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም