በጋምቤላ ላልተፈቱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ይሰራል...ርዕሰ መስተዳደር ጋትሉዋክ ቱት - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ላልተፈቱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ይሰራል...ርዕሰ መስተዳደር ጋትሉዋክ ቱት
ጋምቤላ ሀምሌ 13/2010 በጋምቤላ ክልል ላልተፈቱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በተያዘው አዲሱ በጀት ዓመት በትኩረት እንደሚሰራ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አስታወቁ፡፡ ርዕሰ መስተዳደሩ አቶ ጋትሉዋክ ቱት አጋጥሟቸው ከነበረው የጤና ችግር በተደረገላቸው የሕክምና ድጋፍ ጤናቸው ተመልሶ ወደ መደበኛ ሥራቸው ተመልሰዋል። ርዕሰ መስተዳደሩ አቶ ጋትሉዋክ ቱት በሰጡት ወቅታዊ መግለጫ እንደ አገር እየመጣ ያለውን ለውጥ እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም የህዝቡን የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ተናግረዋል። በክልሉ የተጀመረውን የመንደር ማስባሰብ መርሃ ግብር በማጠናከር ህዝቡን በትምህርት፣ በውሃ፣ በጤና፣ በመልካም አስተዳደርና በሌሎች ልማቶች ይበልጥ ተጠቃሚ የማድረጉ ሥራ የ2011 በጃት ዓመት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑንም ተናግረዋል። በተለይ በማህበራዊና በኢኮኖሚ ዘርፍ ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ የማድረጉ ሥራ በተለየ ሁኔታ ትኩረት እንደሚሰጠው ነወ የገለጹት። አቶ ጋትሉዋክ እንዳሉት ተግባራዊ የበጀት ቀመር በክልሉ ከፍተኛ የበጀት እጥረት ጫና በማሳደሩ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የህዝቡን የልማት ጥያቄ በተፈለገው ፍጥነት መመለስ አልተቻለም። "ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዶክተር አብይ አህመድ በአዲሱ የበጀት ድልድል ታዳጊ ክልሎች ያለባቸውን የበጀት ውስንነት ግምት ውስጥ በማስገባት ለልማት ማስፈፀሚያ ተጨማሪ በጀት መፍቀዳቸው ለክልሎች እድገት ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው" ብለዋል፡፡ እንደርዕሰ መስተዳድሩ ገለጻ በአዲሱ በጀት ዓመት ለክልሉ የተመደበውን በጀት በክልሉ ካለው የሰው ኃይል ጋር በማቀናጀት የተሻለ የልማት ሥራዎችን ለማከናወን ዕቅድ ተይዟል። እንደ አገር የተጀመሩ የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ለውጦችን በክልሉ ተግባራዊ በማድረግ የህዝቡን ተጠቃሚነት በተሻለ ለማረጋገጥ የክልሉ መንግስት እየሰራ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ህዝቡ የሚያነሳቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በማዳመጥ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት እያደረጉት ላለው ጥርት ከፍተኛ አድናቆት እንዳላቸውም አቶ ጋትሉዋክ ገልጸዋል። ያለማንም ሦስተኛ ወገን አደራዳሪነት ከኤርትራ ጋር ሰላም እንዲወርድና የሁለቱ አገራት ህዝቦች ወደ ቀድሞው ውንድማማችነታቸው እንዲመለሱ ማድረጋቸው ለሰላም የሰጡትን ዋጋ እንደሚያሳይ ተናግረዋል። በአገሪቱ ብሎም በክልሉ እየመጣ ያለው ለውጥ ባልተዋጠላቸው ጥቂት ግለሰቦች ለውጡ ወደ ኋላ እንዳይቀለበስ የክልሉ መንግስት ህዝቡን አስተባብሮ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ ባለፉት ሁለት ወራት አጋጥሟቸው የነበረው የጤና ችግር በአገር ውስጥና በውጭ በተደረገላቸው የሕክምና እርዳታ በአሁኑ ወቅት በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኙና መደበኛ ስራቸውን መጀመረቸውን ገልጸዋል።