የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ለመከላከያ ሠራዊት የአንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ለመከላከያ ሠራዊት የአንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 07/2013 (ኢዜአ) የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ለመከላከያ ሠራዊት ያሰባሰበውን የአንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ አስረከበ፡፡
ድጋፉን ያስረከቡት የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ሠራዊቱ የፈፀመው ተግባር መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ያኮራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
“ሠራዊቱ ላከናወነው የጀግንነት ተግባር ያደረግነው ድጋፍ ያንሰዋል” ብለዋል።
በሰራዊቱ ላይ በህወሃት ጁንታ የተፈጸመው የክህደት ጥቃት የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር አባላት በእጅጉ ያስቆጣቸው እንደነበርም አስታውሰዋል።
ክህደት የተፈጸመበት ሰራዊት ራሱን አደራጅቶ የህግ ማስከበር ዘመቻውን አጠናቆ ወንጀለኞችን ወደ ማደን ተግባር መግባቱ የሚያኮራ መሆኑን ገልጸው፤ “የወደፊት ልጆቻችን ይማሩበታል” ብለዋል።
ማኅበሩ ካለው ላይ ቀንሶ ድጋፍ ማድረጉ ለሠራዊቱ ያለውን ክብር ለማሳየት መሆኑን ገልፀዋል።
ዘንድሮ የሚከበረውን 80ኛውን የድል በዓልን ከሠራዊቱ ድል ጋር በማያያዝ በድምቀት ለማክበር በዝግጅት ላይ እንደሚገኝም ጠቁመው፤ ሰራዊቱ አብሮ እንዲያከብር ጥሪ አድርገዋል።
ድጋፉን የተረከቡት የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ማርታ ሉዊጂ ማኅበሩ ከሠራዊቱ ጎን በመቆም ላሳየው ድጋፍ አመስግነዋል፡፡
የሕግ ማስከበር ዘመቻው የመከላከያ ሠራዊቱ የአባቶቹንና የአያቶቹን ጀግንነት የደገመበት ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡