የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ፍቅረሥላሴ ወግደረስ የቀብር ስነ-ስርአት ተፈጸመ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 7/2013 የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ፍቅረ ስላሴ ወግደረስ የቀብር ስነ-ስርአት ዛሬ በመንበረ ጽባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተፈጸመ።

በቀብር ስነ-ስርአቱ ላይ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖትን ጨምሮ የሻምበል ፍቅረሥላሴ ወግደረስ ቤተስቦች፣ የቀድሞ የስራ ባልደረቦች፣ወዳጆቻቸውና ሌሎች ተገኝተዋል።

ፍቅረሥላሴ ወግደረስ የተወለዱት ሐምሌ 7 ቀን 1937 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተለምዶ ቀጨኔ ተብሎ በሚጠራው ሰፈር ነው።

በኢትዮጵያ አየር ኃይል ማሰልጠኛ ወጣት ካዴት ሆነው በመግባት በ1955 ዓ.ም የተመረቁ ሲሆን በአሜሪካ አገርም ስልጠና ወስደዋል።

የ1966ቱ የኢትዮጵያ አብዮት ሲፈነዳ አየር ሃይልን ወክለው የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ አባል እንደነበሩ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በተለያዩ የስልጣን እርከኖች አገራቸውን ያገለገሉት ፍቅረሥላሴ የኢትዮጵያ ሰራተኞች ፓርቲ (ኢሰፓ) አደራጅ ኮሚቴና የደርግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ነበሩ።

ከጳጉሜን 5 ቀን 1979 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 29 ቀን 1982 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን አገልግለዋል።

"እኛና አብዮቱ እና እኔና አብዮቱ” በሚል ርዕስ ሁለት መጽሐፍት ጽፈው ለአንባብያን አድርሰዋል።

ፍቅረሥላሴ ወግደረስ ጨምሮ 42 የደርግ አመራሮች በ1989 ዓ.ም በግድያ፣ በዘር ማጥፋትና በሰብአዊ መብት ጥሰት ወንጀል የተከሰሱ ሲሆን በ2000 ዓ.ም የፍርድ ሂደቱ ሲጠናቀቅ በተከሰሱበት ወንጀል የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው ነበር።

በ2003 ዓ.ም የፍቅረሥላሴንና ሌሎች 23 የደርግ አመራሮች የሞት ቅጣት ተነስቶ በ2004 ዓ.ም ከእስር እንዲፈቱ መደረጉ አይዘነጋም።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በስልጣን ላይ በነበሩበት ግዜ በተለይም የኢትዮጵያ ታሪክ ለትውልድ ተሰንዶ እንዲቀመጥ የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ይታወቁ ነበር።

ፍቅረስላሴ ወግደረስ የሁለት ሴት እና የአንድ ወንድ ልጅ አባት ነበሩ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም