አየር መንገዱ ኮቪድ-19 ዓለም ዓቀፍ ቀውስ ባስከተለበት ወቅት ለነበረው ንቁ አገልግሎት ከኤርባስ የተበረከተለትን የዕውቅና ሽልማት ተቀበለ - ኢዜአ አማርኛ
አየር መንገዱ ኮቪድ-19 ዓለም ዓቀፍ ቀውስ ባስከተለበት ወቅት ለነበረው ንቁ አገልግሎት ከኤርባስ የተበረከተለትን የዕውቅና ሽልማት ተቀበለ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 7/2013(ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኮቪድ-19 ዓለም ዓቀፍ ቀውስ ባስከተለበት ወቅት ለነበረው ንቁ አገልግሎት ከኤርባስ የተበረከተለትን የዕውቅና ሽልማት ተቀበለ።
ሽልማቱን የተረከቡት የኢትዮጵያ አየር መንገዶች ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም “ዓለም በፈለገን ጊዜ ተገኝተናል” ብለዋል።
“ለዚህ ስኬት ላበቁን ከ17 ሺህ በላይ ለሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ሰራተኞቻችንና የማኔጅመንት ቡድን ምስጋናዬን ላቀርብ እወዳለሁ” ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አጋር የሆነው ኤርባስ 350 ለሰጠው ዕውቅናም ምስጋና አቅርበዋል።
የኤርባስ ምክትል ፕሬዚዳንት ሃዲ ሃኩም በበኩላቸው ኤርባስ ለአየር መንገዱ የሰጠው የዕውቅና ሽልማት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ቀውስ ጊዜ ለፈጸመው የማይታመን አገልግሎትና ስኬት ያለውን አድናቆት ለመግለጽ እንደሆነ ተናግረዋል።
“ሌሎች አየር መንገዶች ምን ማከናወን እንዳለባቸው በማሰብ ላይ በነበሩበት ወቅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፍ ብሎ በመብረር ስራውን እየሰራ ነበር” ብለዋል። አየር መንገዱ መፍትሄ አፍልቆ ስራ ላይ እንደነበር አስታውሰዋል።
“የመንገደኞች አውሮፕላኖችን የጭነት ማጓጓዣ በማድረግ ሰርተዋል” ሲሉ የአየር መንገዱን የስኬት ጉዞ አስታውሰው፤ “ይህ ደግሞ በመላው ዓለም ልዩ የሚያደርገው ነው ብለዋል።
ሌሎች አየር መንገዶች የአቅማቸውን 10 በመቶ ያህል ለመንቀሳቀስ ሲሞክሩ የኢትዮጵያ አየር መንገዱ በሙሉ አቅሙ እየሰራ መሆኑን መስክረው፤ ሌሎች አየር መንገዶች ሰራተኞቻቸውን ለመቀነስ መገደዳቸውንና ኪሳራ እንዳጋጠማቸው ገልጸዋል።
የአየር መንገዱ ስኬት የመነጨው ከአመራሮቹ ባለራዕይ መሆን እንደሆነም መናገራቸውን ኢዜአ ከለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘው መረጃ ያሳያል።