ቀጥታ፡

የህወሓት ጁንታ ባለፉት ሁለት ዓመታት የሳይበር ጦረኞችን በማሰማራት አገር ለማተራመስ ብዙ ጥሯል… የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 7/2013(ኢዜአ) የህወሓት ጁንታ ባለፉት ሁለት ዓመታት ተከፋይ የሳይበር ጦረኞችን አሰማርቶ ሃሰተኛ መረጃ በማሰራጨት አገር ለማተራመስ በርካታ ጥረት ማድረጉን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ አስታወቀ።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛው በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት ጁንታው ከሆነለት ወደ ስልጣን ዳግም ለመመለስ ካልሆነም ኢትዮጵያን ለማፍረስ ባለፉት ሁለት አመታት በርካታ የጥፋት ሙከራዎችን አድርጓል።

ለዚህም በርካታ ተከፋይ የሳይበር ጦረኞችን በማሰማራት ሃሰተኛ መረጃ በማሰራጨት አገር ለማተራመስ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል ነው ያሉት። 

የጁንታው ቡድን አቅዶና ተዘጋጅቶ በሚያከናውናቸው ስውር ወንጀሎች በተላላኪዎቹ የተለያዩ ጥፋቶችን መፈፀሙን ገልጸዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች እንዲቀሰቀሱና ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር በማድርግም በርካታ ጥረቶች ማድረጉን አስታውሰዋል።

የህወሃት ጁንታ የማህበራዊ ትስስር ገጾችን ተጠቅሞ በተከፋዮቹ በኩል ብሄር ተኮር ሃሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨት ውዥንብር ሲፈጥር መቆየቱንም ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች ግጭት በመቀስቀስ፣ አለመረጋጋት እንዲኖርና በዜጎች መካከል እርስ በእርስ አለመተማመን እንዲኖር ሲሰራ ቆይቷልም ነው ያሉት።

የጥፋት ቡድኑ ቀድሞ ከአገር በዘረፈው ሀብት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ መድቦ አገር ለማፍረስ ሲሰራ እንደነበርም ነው ዶክተር ሹመቴ የገለጹት።

በተለያዩ አገራት "ጋዜጠኞችንና ተሰሚነት ያላቸው የፖለቲካ ተንታኞችን በመቅጠር" የሀሰት መረጃዎችን በማሰራጨት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ላይ የተዛባ መረጃ እንዲደርሰው ለማድረግ ብዙ ጥረት ማድረጉንም ተናግረዋል።

ከጁንታው ጋር የጥቅም ትስስር ካላቸው የውጭ ዜጎች መካከል አንዱ የሆነው ጄቲን ትሮንቮልት ከሚያሰራጨው ሃሰተኛ መረጃ በተጨማሪ ሌሎች የኢትዮጵያን መበታተን ከሚፈልጉ ጋር በዌቢናር ውይይት እስከማካሄድ የደረሰ መሆኑንም ዶክተር ሹመቴ ገልጸዋል። 

የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲህ አይነት እኩይ አላማ አንግበው ለጥቅማቸው በመገዛት ለጥፋት የሚሰሩ አካላትን የተሳሳተ መረጃ መቀበል እንደሌለበትም አስገንዝበዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም ሰሞኑን ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት በ14 ቀናት ውስጥ ብቻ በመንግስት ተቋማት፣ በትምህርት፣ በፋይናንስ፣ በመገናኛ ብዙሃን እና በቴሌኮም መሰረተ ልማት ላይ ያነጣጠረ 39 ነጥብ 8 ቢሊዮን ጊዜ የሳይበር ጥቃት ሙከራ ተፈፅሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም