የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሠራተኞች ለገበታ ለአገር እና ለሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክቶች ድጋፍ አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሠራተኞች ለገበታ ለአገር እና ለሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክቶች ድጋፍ አደረጉ
አዲስ አበባ ታህሳስ 7/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሠራተኞችና አመራሮች ለገበታ ለአገር ፕሮጀክትና ለታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከወር ደመወዛቸው ድጋፍ አደረጉ።
ከተቋቋመ 79 ዓመት ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት /ኢዜአ/ በመላ አገሪቷ ባሉት 36 ቅርንጫፎቹ ዜና እና ዜና ነክ መረጃዎችን በማሰባሰብ ለመገናኛ ብዙሃንና ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ያደርጋል።
ተቋሙ በዋናነት መረጃዎች በተለያዩ ቋንቋዎች ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ከማድረግ በተጨማሪ በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮችም ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው።
የተቋሙ ሠራተኞችና አመራሮች ከወር ደመወዛቸው ለአገራዊ ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ የሚውል ገንዘብ በመስጠት ድጋፋቸውን ማጠናከራቸው አንድ ማሳያ ነው።
ሠራተኞቹና አመራሮቹ ለገበታ ለአገር ፕሮጀክት ከ141 ሺህ ብር በላይ፤ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብም ከ138 ሺህ ብር በላይ ቦንድ በመግዛት ተሳትፈዋል።
የተቋሙ የሕዝብ ግኑኙነትና ስትራቴጂካዊ አጋርነት ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ ወንድይራድ እንደገለፁት የተቋሙ ሠራተኞች ለገበታ ለአገር ፕሮጀክትና ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክቶች እንዲውል በድምሩ 278 ሺህ ብር ከወር ደመወዛቸው ላይ ድጋፍ አድርገዋል።
ዳይሬክተሩ እንዳሉት ተቋሙ በዋናነት በማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አጀንዳዎች ላይ ለማኅበረሰቡ ወቅታዊና አስተማማኝ መረጃ በማድረስ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል።
ለዚህም በተለይ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ከተከሰተ ጀምሮ በጤና ሚኒስቴር ቋሚ ዘጋቢዎችን በመመደብ ወቅታዊ መረጃዎችን ለመገናኛ ብዙሃንና ለኅብረተሰቡ ሲያደርስ መቆየቱን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
መንግስት በቅርቡ በወሰደው የሕግ ማስከበር ዘመቻና አሁን እያከናወና ባለው የሰብዓዊ ድጋፍ ባለሙያዎቹን ወደ ስፍራው በመላክ ወቅታዊና አስተማማኝ መረጃዎችን ለሕዝብ ተደራሽ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢዜአ ሠራተኞችና አመራሩ በአገራዊ ጉዳዮችም ሆነ በማኅበራዊ ጉዳይ ኃላፊነታቸውን በመወጣት ላይ መሆናቸውንም ነው አቶ ዮሐንስ የተናገሩት።
እንደ እርሳቸው ገለጻ የተቋሙ ሠራተኞችና አመራሮች በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብርም ችግኞችን በመትከልና መንከባከብ እየሰሩ ይገኛሉ።
በበጎ ፍቃድ አገልግሎትም ከብሔራዊ የደም ባንክ ጋር በመተባባር የተቋሙ ሠራተኞች በየሦስት ወሩ የደም ልገሳ ያደርጋሉ።
ሠራተኞቹና አመራሮቹ ተቋሙ በሚገኝበት አካባቢ ለሚኖሩ ወላጆቻቸው በአነስተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ ተማሪዎች በቋሚነት የምግብ፣ የንጽህና መጠበቂያና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ እደሚያደርጉ አስረድተዋል።
የተቋሙ ሠራተኞች ቀደም ሲልም ለአገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች ድጋፍ ማድረጋቸውን ያስታወሱት አቶ ዮሐንስ የሕዳሴው ግድብ የኢትዮጵያ ሕዝብ ታላላቅ የልማት ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም ገንብቶ መጨረስ እንደሚቻል ለዓለም ያሳየበት መሆኑን ጠቅሰዋል።