ወጣቱ ውትድርና የሚያኮራ ሙያ መሆኑን በመገንዘብ ተሳትፎውን ሊያጠናክር ይገባል- የሪፐብሊካን ጋርድ ተመራቂዎች - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቱ ውትድርና የሚያኮራ ሙያ መሆኑን በመገንዘብ ተሳትፎውን ሊያጠናክር ይገባል- የሪፐብሊካን ጋርድ ተመራቂዎች
ሐዋሳ ታኀሳስ 6/2013 (ኢዜአ) ወጣቱ ውትድርና የሚያኮራ ሙያ መሆኑን በመገንዘብ ተሳትፎውን ሊያጠናክር እንደሚገባ የሪፐብሊካን ጋርድ መሠረታዊ ኮማንዶ ተመራቂዎች አስገነዘቡ።
የ33ኛ ዙር የሪፐብሊካን ጋርድ መሠረታዊ ኮማንዶ ተመራቂዎች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት "ሀገርንና ወገንን በውትድርና ሙያ ማገልገል ታላቅ ክብር ነው" ብለዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል መሠረታዊ ኮማንዶ ጫላ ጋርደው እንዳለው የሀገርንና የህዝብን ሰላምና ደህንንት የሚጠብቅና የሚያስከበር ወታደሪያዊ ኃይል ያስፈልጋል።
"አሁን ላይ ወጣቱ ለውትድርና ሙያ ያለው ፍላጎት አነስተኛ ሊሆን የቻለው በማህበረሰቡ ውስጥ ባለው የተዛባ አመለካከት ነው" ብሏል ።
ወጣቶች ውትድርና ለሀገርና ለህዝብ መኖርን የሚጠይቅ ታላቅ ኃላፊነትን መቀበል መሆኑን በመረዳትና አርቆ በማስተዋል ሀገራቸውን በሙያው እንዲያገለግሉ አስገንዝቧል።
መንግሥት ለውትድርና ስራው ፍቅር ያላቸው ወጣቶችን ለመሳብና ዘርፍን ተመራጭ ለማድረግ አበክሮ መስራት እንዳለበት አመላክቷል።
መሠረታዊ ኮማንዶ ታጁር ተፈራ በበኩሏ "ሴትነት በውትድርና ሙያ ተሰልፎ ሀገርንና ህዝብን ከማገልገል አያግድም" ብላለች።
በ2009 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ውትድርናን መቀላቀሏን ያስታወሰቸው ታጁር ከእግረኛ ክፍለ ጦር ተመልምላ የኮማንዶ ስልጠና ለመውሰድ በመብቃቷ መደሰቷን ገልፃለች።
በቆይታዋ ውትድርና አስደሳች ሙያ ሆኖ እንዳገኘቸው በመግለፅ እህት ወንድሞቿን ጨምሮ ማንኛውም ወጣት ዘርፉን እንዲቀላቀል ምክሯን ለግሳለች።
ወታደር ሲኮን የግዳጅ ኃላፊነት ስላለው አስፈሪ የሆነ ገፅታ እንዳለው የገለጸው ደግሞ መሠረታዊ ኮማንዶ የሺአምበል ሙሉ አስፋው ነው።
"ነገር ግን ወታደሪያዊ ማሰልጠኛ ጣቢያ ስገባ ስነ ልቦናዊ ጥንካሬ እንዲኖረኝና ሙያውን እንድወድ አድርጎኛል" ብሏል።
በተለይ ወታደር መሆን ጠንካራ የአካል ብቃት፣ የሀገርና የህዝብ አለኝታና የቁርጥ ቀን ልጅነትን ከማጎናፀፉ ባሻገር ክብርም መታደልም ስለሆነ ወጣቶች ሙያውን ተቀላቅለው እንዲያገለግሉ ጥሪ አቅርቧል።
በውትድርና ሙያ ለማገልገል ፍቃደኛ የሆኑ ወጣቶችን ለማግኘት መንግሥት ከባድ እንደሆነበት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ በቅርቡ ለህዝብ ተወካዮች ምከር ቤት ባቀረቡት ሪፓርት ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመት የውትድርና መስፈርቱን የሚያሟሉ ተመዝጋቢዎች ሰፊ የህዝብ ቁጥር ካላቸው ኦሮሚያና አማራ ክልልች ለማግኘት የሀገር መከላከያ ሠራዊት አዳጋች እንደሆነበትም ተናግረው ነበር።
በመሆኑም የኢትዮጵያ ህዝብ በጉዳዩ ላይ እንዲያስብበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አፅንዖት መስጠታቸው ይታወቃል።
በብላቴ የሚገኘው የልዩ ዘመቻዎች ኃይል ማሰልጠኛ ማዕከል ለ33ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን የሪፐብሊካን ጋርድ መሠረታዊ ኮማንዶ አባላት ሰሞኑን ማስመረቁን ኢዜአ መዘገቡ ይታወሳል።