ቀጥታ፡

መንግስት በትግራይ ክልል ያሰራጨው መድሃኒት ለታካሚዎች እፎይታ ፈጥሯል - የህክምና ባለሙያዎች

አዲስ አበባ ታህሳስ 7/2013 (ኢዜአ) መንግስት በትግራይ ክልል ያሰራጨው መድሃኒት ለታካሚዎች እፎይታ መፍጠሩን የህክምና ባለሙያዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ ለትግራይ ክልል የላካቸው መድሃኒቶች ለታካሚዎች እፎይታን የሰጡ፣ ሃኪሞችንም ከጭንቀት የገላገሉ መሆናቸውን የህክምና ባለሙያዎች ገለጹ፡፡

ኤጀንሲው ወደ ትግራይ የላካቸው መድሃኒቶች እና የህክምና ቁሳቁሶች በመቀሌ ከተማ ለሚገኙ የተለያዩ የጤና ተቋማት በመሰራጨት ላይ ናቸው።

ለኢዜአ አስተያየታቸው የሰጡ የህክምና ባለሙያዎች ቀደም ሲል በከተማዋ የመድሃኒት አቅርቦት በመስተጓጎሉ ህሙማን ለከፍተኛ ጭንቀት ተዳርገው እንደነበር ተናግረዋል፡፡

በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የዓይደር ኮምፕሬሄንሲቭ እስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የመድሃኒት ቤት ሃላፊ ሃሊማ አህመድ ከፌደራል መንግስት የተላኩ የተለያዩ መድሃኒቶችን መረከባቸውን ገልጸዋል፡፡ 

የመድሃኒት አቅርቦቱ ሆስፒታሉ የነበረበትን የመድሃኒት እጥረት ችግር የሚፈታ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

የሆስፒታሉ ፋርማሲስት አበባ ገብረሚካኤል፤ህሙማን ከሆስፒታሉ በነጻ የሚያገኟቸውን መድሃኒቶች ከውጪ በውድ ዋጋ ሲገዙ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ 

አሁን ግን መንግስት በድሃኒቶቹን በማቅረቡ ችግሩ መፈታቱን ተናግረዋል።

የመድሃኒት አቅርቦቱ የታካሚዎችን ችግር ከመፍታት በተጨማሪ ሃኪሞችም ለማህበረሰቡ በቂ አገልግሎት እንዲሰጡ ያስችላል ብለዋል።

የፌዴራል መንግስት በአስቸኳይ መሰረተ ልማቶችን በመጠገን ለክልሉ ህዝብ የመድሃትና የህክምና ቁሳቁስ አቅርቦት በማሟላቱ የህክምና ባለሙያዎቹ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የፌደራል መንግስት ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸውን መድሃኒቶችን በመቀሌ ከተማ ለተለያዩ የጤና ተቋማት ማሰራጨቱ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም