ሞተር አልባ ትራንስፖርት በኢትዮጵያ - ኢዜአ አማርኛ
ሞተር አልባ ትራንስፖርት በኢትዮጵያ
አየለ ያረጋል (ከኢዜአ)
መግቢያ
ኢትዮጵያ ዝቅተኛ የካርቦን ልቀት ያላት አገር ናት። በተለመደው የዕድገት አቅጣጫ ከቀጠለች ግን የካርቦን ልቀቱ መጠን መጨመሩ አይቀሬ ነው። ኢትዮጵያ ከካርቦን ልቀት ነጻ የሆነ የዕድገት አቅጣጫ ለመከተል እንደወሰነች ደጋግማ አሳውቃለች። ይህ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ዋና ዋና ምሰሶዎች ግብርና፣ ደን ልማት፣ ታዳሽ ሃይል እንዲሁም ሃይል ቆጣቢ አዳዲስ ስሉጥ ቴክኖሎጂዎችን በትራንስፖርት፣ በኢንዱስትሪና በህንጻ ግንባታዎች መተግበር የሚሉ ናቸው።
በዚህ ጽሁፍ የምናነሳው ዘመናዊና ኃይል ቆጣቢ የማጓጓዣ ቴክኖሎጂዎችን ነው። ከተሞችና የገጠር ማዕከላት እድገታቸው በጨመረ ልክ የትራንስፖርት አገልግሎት ፍላጎት እያደገ ይመጣል። ከትራፊክ መጨናነቅና መልከ ብዙ አደጋዎች ባሻገር የአካባቢ አየር ብክለት ችግርም ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ነው። እናም ዓለም በተሽከርካሪዎች ካርበን ልቀት እየተበከለች ባለችበት በዚህ ዘመን የሞተር አልባ ትራንስፖርት ቀዳሚው የትኩረት አቅጣጫ እየሆነ መጥቷል።
በርካታ ያደጉ አገራት ከአነስተኛ ተሽከርካሪ እስከ ባቡርና በኤሌክትሪክ የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎችን እየተገለገሉ ነው። የትራንስፖርቱን ዘርፍ ሙሉ ለሙሉ ነዳጅ አልባ ለማድረግም የሚሰሩም አሉ። በዚህም አገሮቹ ከመኪናዎች የሚወጣ በካይ ጋዝን ከማስቀረት ጎን ለጎን የድምፅ ብክለትን ቀንሰዋል፤ በተመጣጣኝ ዋጋም ዜጎችን ተጠቃሚ አድርገዋል። ለምሳሌ ቻይና፣ ጃፓን፣ ህንድንም ጨምሮ ሌሎች የእስያ አገራት በሞተር አልባ ትራንስፖርት ስትራቴጂ እየተመሩ ነው። አገሮቹ የሕግ ማዕቀፍ ከማስቀመጣቸው በተጨማሪ መሠረተ ልማቶች ሲከናወኑ ሞተር አልባ ትራንስፖርትን ከግንዛቤ ውስጥ እንዲገባ አድርገዋል፡፡
አገሮቹ በኤሌትክሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን ለሚገዙ ደንበኞች መንግሥት ገሚሱን ወጪ እንዲሸፍንም አሠራር ዘርግተው ኅብረተሰቡ ተጠቃሚ አድርገዋል። የሞተር አልባ ትራንስፖርት አገልግሎት የከባቢ አየር ብክለትን ሙሉ በሙሉ የሚያስቀር፣ ፍጥነቱ አነስተኛ በመሆኑም የትራፊክ አደጋን ከመቀነስ አንፃር ጉልህ ሚና አለው፡፡
በኢትዮጵያ 69 ከተሞች የሞተር አልባ ትራንስፖርትን ለመዘርጋት እየተሰራ ነው - ትራንስፖርት ሚኒስቴር
ኢትዮጵያ የትራንስፖርት እንቅስቃሴን ለማሻሻልና ሁሉን አቀፍ ልማትን ለማረጋገጥ የአስር ዓመት የሞተር አልባ ትራንስፖርት ስትራቴጂን ቀርጻለች። ከ2013 እስከ 2022 ዓ.ም የሚተገበረው ብሔራዊው የሞተር አልባ ትራንስፖርት ስትራቴጂ በሦስት ዓመት የትግበራ እቅድ የሚታገዝ ሲሆን ዓመታዊ የእንቅስቃሴ እቅዶችን መስመር የሚያስይዝና የሞተር አልባ ትራንስፖርት መሰረተ ልማት መዋዕለ ንዋይ ፍሰትን የሚመራ ይሆናል፡፡ ለእያንዳንዱ እንቅስቃሴ የትግበራ እቅዱ ኃላፊነቱን የሚወስደውን ተቋም የጊዜ ገደብ እና የበጀት ግምት ያስቀምጣል፡፡
በትራንስፖርት ሚኒስቴር የሚኒስትሩ ከፍተኛ አማካሪ አቶ ጋሻው ጠና እንደሚሉት ስትራቴጂው የወጣው የመንገድ መሰረተ ልማት ዝርጋታና የትራንስፖርት አገልግሎት ተፈጥሯዊ ሥነ ምህዳርን ጠብቆ እንዲራመድ፣ ዘመናዊ፣ ፈጣን፣ ወጪ ቆጣቢና ተደራሽ የትራንስፖርት መሰረተ ልማት ለመገንባት ያለመ ነው። በመንገድ ደህንነትና አካባቢ ጥበቃ አንጻር ከዓለም አቀፍና አገር አቀፍ አጋር ተቋማት ጋር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። በቀጣይ 10 ዓመታት ገቢራዊ የሚደረገው ስትራቴጂው ሞተር አልባ ትራንስፖርትን በሦስት አይነት ከፋፍሎ አስቀምጧል ይላሉ።
የመጀመሪያው እግረኛና የሳይክል ትራንስፖርት ነው። በታሪክ ከተሞች ሲገነቡ መሃንዲሶች የመኪናን እንጂ የእግረኛ መንገድ ትኩረት ሳይሰጠው እንደቆየ ይገልጻሉ። አዲስ አበባን ጨምሮ በኢትዮጵያ ከተሞችም ይህ መንገድን ለተሽከርካሪ እንጂ ለሰው ታሳቢ ሳይደረግ እስከዛሬ መምጣቱን ይናገራሉ። በኢትዮጵያዊያን ታሪክ የእግረኛ መንገድ ለ6 ወይም ለ7 ሺህ ዓመታት የነበረ በገበያም ሆነ በሌላ ማህበራዊ ትስስር መድረኮች ሰዎችን የሚያገናኝ ትራንስፖርት አይነት እንደሆነ ይገልጻሉ።
በአንጻሩ የመኪና ታሪክ በመቶ ሀያ ዓመት ያልበለጠ እድሜ ያለው ቢሆንም መሃንዲሶች ግን መንገድን ለመኪና ብቻ አስበው ሲሰሩ እንደነበር ገልጸዋል። እናም ቀዳሚ ስራችን የእግር ጉዞ ለምሳሌ እንደ አንድ የትራንስፖርት አይነት በመሆኑ ግንዛቤ ፈጠራ ላይ እየተሰራ ነው ይላሉ። ከጳጉሜን እስከ ጳጉሜን የእግር ጉዞን ጨምሮ በርካታ ሁነቶችም ማካሄዳቸውን አንስተዋል። ‘መንገድ ለተሽከርካሪ’ ከሚው እሳቤ ይልቅ ‘መንገድ ለሰው’ የሚለው ቅድሚያ እንደተሰጠው ያብራራሉ አማካሪው አቶ ጋሻው። የአውሮፓ አገራት የመኪና መስመሮችን ወደእግረኛ እየመለሱ መሆኑን በማንሳት መንገዱን ወደእግረኛ መለወጥ ላይ በኢትዮጵያም እንደተተኮረ ተናግረዋል።
ከግንዛቤ ፈጠረው ባሻገር ደግሞ ደህንነቱን የተጠበቀ ዝርዝር የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች ላይ መተኮሩን ገልጸዋል። ለአብነትም በቀጣይ 3 ዓመት በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ 300 ኪሎ ሜትር ለእግረኛ እንዲሁም 200 ኪሎሜትር ለሳይክል መሰረተ ልማት ለመገንባት ዕቅድ መያዙን ነው ያብራሩት። በሁሉም ከተሞች እግረኛው የሚራመድበት፣ ባለሳይክሉም የሚያሽከረክርበት የራሳቸው መንገድ በመዘርጋት አሁን ላይ የሚስተዋለውን የተሽከርካሪና የሰው ዘፈቀዳዊ እንቅስቃሴ ለመለወጥ ስራ መጀመሩንም አንስተዋል።
አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ መሰረት በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠሩ የባቡር ሃዲድ መስመሮችን፣ አውቶቡሶችን በመዘርጋት የማጓጓዣውን ብክለት መቀነስ፤ ከውጪ የሚገዛውን ቤንዚን ከሸንኮራ አገዳ በአገር ውስጥ በሚመረት አልኮል እንዲተካ እና ናፍጣንም በአገር ውስጥ ከዕፀዋት በሚመነጭ ዘይት መቀየር የሚል አማራጭም አለ። የነዳጅ የተጠቃሚ መኪኖችን በኤሌክትሪክ ኃይል መተካት፣ በኤሌክትሪክና በነዳጅ ኃይል ጥንቅር የሚሠሩ አዳዲስ መኪኖች ወደስራ በማስገባት የነዳጅ አጠቃቀምን ማሻሻል፤ በመኪና ማጓጓዝን ለመቀነስ አገር አቋራጭ የኤሌክትሪክ ሃዲድ መጓጓዣ መስመሮችን መዘርጋት ኢትዮጵያ ከያዘቻቸው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ዕቅዶች መካከል ይገኙበታል።
በ10 ዓመቱ ስትራቴጂ ከ50 ሺህ በላይ ነዋሪ ያላቸው 69 የኢትዮጵያ ከተሞች የሞተር አልባ ትራንስፖርት ስርዓት ለመተግበር ታቅዷል። ይህም የከተሞች የትራስፖርት ችግር በመቅረፍ ዘላቂና ታዳሽ በሆኑ የትራንስፖርት አማራጮች ለመተካት ያለመ ነው። የዚህ ሕግ ማዕቀፍና ዝርዝር ማስፈጸሚያ ስልቶችም ጎን ለጎን እየተዘጋጁ መሆኑን አማካሪው ተናግረዋል።
ሁለተኛው በስትራቴጂው ትኩረት የተሰጠው የትራንስፖርት አማራጭ ደግሞ የህዝብ ትራንስፖርት ነው። አቶ ጋሻው “60 ትናንሽ መኪኖች አቁመህ በአንድ አውቶቢስ ብትሄድ የሚተርፈውን መንገድ ማሰብ ትችላለህ። ስለዚህ ቀጣይ ትኩረት የተሰጠው ዘመናዊ የህዝብ ትራንስፖርት ላይ ነው። ይህም ከአካባቢ ብክለትና ከቦታ አጠቃቅም አኳያ አዋጭ ነው” ብለዋል። በስትራቴጂው መሰረት ከተጀመሩ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የፈጣን ባስ ትራንስፖርት እንደሆነ ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ከዊንጌት እስከ ጀሞ የሚገነባው የአውቶቡስ መስመር ለአብነት የነሳሉ። ይህ ከዊንጌት ተነስቶ ጀሞ ለመድረስ ረጅም ኪሎሜትሮችን በአጭር ደቂቃዎች ማድረስ የሚችል፣ የከተማውን 40 በመቶ ህዝብ በዚያ መስመር ብቻ ማስተናገድ እንደሚችል ገልጸዋል። በቀጣይም ሰባት የፈጣን አውቶቢስ መስመሮች በአዲስ አበባ እንደሚገነቡ ተናግረዋል። ይህ የህዝብ ትራንስፖርት አማራጭም በካርበን ልቀት የሚያመጣው ተጽዕኖ የቀነሱ መሆኑን ይናገራሉ።
ፈጣን የከተማ አውቶቡስ ከከተማ ከቀላል ባቡር የተሻለ አማራጭ እንደሆነም ገልጸዋል። ወጣ ገባ መልክዓ ምደር በሚበዛባቸው በኢትዮጵያ ከተሞቸም ቀላል ባቡር ከግንባታ ወጭ አንጻር አሉታዎ ተጽዕኖ እንዳለው ገልጸዋል። የአዲስ አበበ ቀላል ባቡርን ለአስረጂነት በማንሳት ነዋሪዎችን በስራ አካባቢ የነጣጠለ ሁኔታ መፍጠሩን በማሳያነት አንስተዋል። ስለሆነም ባቡር ታዳሽ ሃይል ቢሆንም የህዝብ ትራንስፖርትን ያህል ግን ተመራጭ እንዳልሆነ አስረድተዋል። ኢትዮጵያ በቀጣይም ስድስት ዓመታት የተጀመሩ የባቡር መስመሮቹን ማጠናቀቅ ካልሆነ በስተቀር ሌሎች አዳዲስ መስመሮቹን እንደማትገነባም አረጋገጠዋል። ከዛም በኋላ ቢሆን የቦታዎች የኢኮኖሚ ጠቀሜታና ከአገሪቱ ሀብት አንጻር አዋጭነታቸው ተጠንቶ እንደሆነ ተናግረዋል።
ከመጀመሪያና ሁለተኛው የትራንስፖርት አማራጭ በኋላ የሚመጣው ሌላው የመኪና ትራንስፖርት አማራጭ ነው። ኢትዮጵያ በቀጣይ 10 ዓመታት 245 ሺህ ኪሎ ሜትር የመንገድ መሰረተ ልማት ለመዘርጋት ማቀዷን ያወሳሉ። ይህ መሰረተ ልማት ሲታሰብ በከተሞች ለእግረኛና የተሽከርካሪን መንገድን ታሳቢ ያደረገ እንደሚሆን ገልጸዋል። “ትልቁ ዓላማችን ታዳሽ ሃይል ላይ ነው። ከድምጽና ከአካባቢ ብክለት፣ ከጤና አኳያ ብዙ ጥቅም ስላለው ነው” ይላሉ።
የግል ዘርፍ ተሳትፎ በሞተር አልባ ትራንስፖርት
በአዲሱ ስትራቴጂ የመንግስት ሚና ህግ ማዕቀፍ ማውጣትና የስራ ሜዳን መፍጠር እንደሆነ አቶ ጋሻው ያነሳሉ። በሞተር አልባ ትራንስፖረት ዘርፍ ሜዳው እንዲገባ የግል ዘርፉ ይበረታታል።
እስካሁን በሞተር አልባ ትራንስፖርት ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶች (ለምሳሌ ቶምኢባይክ እና ማራቶን ሞተርስ) ተሽከርካሪዎቹ በመገጣጠማቸው የእውቀት ሽግግር እየፈጠሩ መሆኑን ያነሳሉ። በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ሞተር ሳይክሎች፣ የቆሻሻ መጣያዎች፣ እየተንቀሳቀሱ የመኪና እጥበት አገልግሎት የሚሰጡ ማሽኖች፣ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ ተሽከርካሪ፣ ማረሻ፣ ማረሚያ፣ የቤት መኪና፣ በኤሌክትሪክ የሚሠራ ኤፍ.ኤስ አር እና ሌሎች ተሽከርካሪዎችን የሚያመርቱና የሚገጣጥሙ ድርጅቶች አሉ።
ያም ሆኖ የሞተር አልባ ተሽከርካሪዎችን ታሳቢ ያደረገ የሕግ ማዕቀፍ አለመኖር ችግር እንዳለ አንስተዋል። በሕንፃዎች ላይ የኤሌክትራክ ቻርጅ አገልግሎት፣ የኤሌክትሪክ ታሪፍ፣ ከባንኮች ጋር ለመሥራት መመሪያዎች፣ ለሞተር አልባ ትራንስፖርት የሚሆኑ መንገዶችና ሌሎችም ተያያዥ ሥራዎች ማሟላት እንደሚገባም ይናገራሉ።
በጉዳዩ ላይ ሃሳብ የሰጡት አቶ ጋሻው እንዳሉት የአውቶሞቲቭ ፖሊሲ ለማውጣት ስራ መጀመሩን ገልጸዋል። በቅርቡ ከሞተር አልባ ተሽከርካሪ አስመጪዎች ጋር በጋራ ለመስራት ውይይት መደረጉን፤ የሕግ ማዕቀፍ ለማውጣትም ሃሳብ ማዋጣታቸውን ይገልጻሉ። በቀጣይም በቋሚነት ውይይትና ምክክር በማድረግ ችግሮችን ለመፍታት መስማማታቸውን ተናግረዋል።
በ10 ዓመቱ የግሉ ዘርፍ በኤሌክርቲክ ትራንስፖርት በሰፊው እንዲገባና ሞተር አልባ ትራንስፖርት ራሱን የቻለ ኢንቨስተመንት ዘርፍ ሆኖ እንዲወጣ ታልሟል። የሚያስመጡና የሚገጣጠሙ ድርጅቶችን እናበረታታለን። በቅርቡ ደግሞ የውጭ ኢንቨስትመንት መድረክ በትራንስፖርት ዘርፍ እንደሚደረግና ዘርፉን ለግል ድርጅቶች ከፍት ለማድርግ የማስተዋወቅ ስራዎች እንደሚያከናወኑ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኤሌክትሪክ የሚሠራ፣ የካርቦን ልቀት የማያስከትለውንና የሀዮንዳይ ኩባንያ አካል በሆነው ማራቶን ሞተርስ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ የተገጣጠመውን መኪና በስጦታ በተረከቡበት ወቅት፣ ቴክኖሎጂው በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋምና ለአረንጓዴ ልምላሜ ከፍተኛ ድጋፍ እንደሚያደርግ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
መውጫ
ሞተር አልባ ትራንስፖርት ተደራሽ ህዝባዊ እንቅስቃሴን ከማጎናፀፉ ባሻገር በጤናው መስክም ትልቅ ፋይዳ አለው። ሞተር አልባ መጓጓዣ የጉዞ ደህንነት ያስገኛል። በግል ተሽከርካሪ ከመጠቀም ይገላግላል። ይህ ደግሞ የከተሞችን ትራፊክ መጨናነቅን ያቃልላል። በርግጥ የኢትዮጵያ ከተሞች ግን የሞተር አልባ ትራንስፖርት ታሳቢ አድረገው ባለመገንባታቸው ይህን አይነት ዘዴ ገቢራዊ ለማድረግ ፈታኝነት አለው። መረጃዎች እንሚጠቁሙት የመንገድ ዲዛይኖቹ ከእግረኛ ይልቅ ለተሽከርካሪ ትኩረት ሰጥተው በመገንባታቸው የህዝብ መራራቅ ነፍጓል፤ የአኗኗር ጥራት እንዳይኖር አድርጓል። በእግር ጉዞ፣ በሳይክልና በህዝብ ትራንስፖርት ዕቅድ፣ ዲዛይን፣ ግንባታና የትራንስፖርት ስርዓት ስራ አመራር ይበልጥ የመንገዶቹን ስፋት ታሳቢ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።